ተመድ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት በአፍሪካ ታይቶ የማይታወቅ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ሲል አስጠነቀቀ
በከተሞች አካባቢ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች በኑሮ ውድነቱ ሳቢያ ወደ አምጽ ሊያመሩ ይችላሉ
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት እስከ 80 በመቶ የሚሆነውን ስንዴ ፍጆታ ከሩሲያና ከዩክሬን ነው የሚገዙት
በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለውን ጦርነት ተከትሎ በተከሰተው የነዳጅ እና የምግብ ዋጋ መወደድ በአፍሪካ 'ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ' ቀውስ ሊያስከትል እንደሚችል የተባበሩት መንግስታት ድርጅት አሳሰበ።
በዩክሬን እየተካሄደ ያለው ጦርነት እና ምእራባውያን በሞስኮ ላይ እየጣሉት ያለው መጠነ ሰፊ ማዕቀብ ስንዴ እና ማዳበሪያን ጨምሮ የሌሎች ምርቶች አቅርቦትን እያስተጓጎለ ነው ያለው ተመድ፤ ይህም በአፍሪካ ላይ ተጨማሪ አደጋ መደቀኑን ነው ያስታወቀው።
የጠመደ የልማት ፕሮግራም የአፍሪካ ኃላፊ ራይመንድ ግሊፒን በትናትናው እለት በስጡት አስተያየት፤ የዩክሬን ሩሲያ ጦርነት በአፍሪካ ከዚህ በፊት ታይቶ የማያውቅ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል ብለዋል።
ኃላፊው ራይመንድ ግሊፒን፤ አሁን እያጋጠሙ ያሉ የኢኮኖሚ ችግሮች በአህጉሪቱ ከፍተኛ የሆነ ማህበራዊ ቀውስችን እያስከተሉ መሆኑን ተናግረዋል።
በተለይም በከተሞች አካባቢ ያለው ውጥረት ከፍተኛ ነው ያሉት ግሊፒን፤ ዝቅተኛ ገቢ የሚያገኙ የህብረተሰብ ክፍሎች አሁን ያለው ቀውስ ወደ አምጽ እና ግጭት እንዲያመሩ ሊያስገድዳቸው እንደሚችል ስጋታቸውን አስቀምጠዋል።
በተለይም በዘንድሮው ዓመት እና በቀጣይ ዓመት ምርጫን የሚያደርጉ ሀገራት ከኑሮ ውድነት ጋር ተያይዘው ለሚቀሰቀሱ አመጾች ተጋላጭ መሆናቸውንም አስታውቀዋል።
በርካታ የአፍሪካ ሀገራት ከፍተኛ የስንዴ ላኪ ሀገራት በሆኑት ከዩክሬን እና ከሩሲያ በሚገቡ ምግቦች እና ማዳበሪያ ላይ ጥገኛ መሆናቸው ይታወቃል።
በተለይም በርከት ያሉ የአፍሪካ ሀገራት ከሚያስፈልጋቸው የስንዴ ፍጆታ ውስጥ 80 በመቶውን ከሩሲያ እና ከዩክሬን እንደሚገዙ መረጃዎች ያመለክታሉ።
ጦርነቱ ከምግብ ፍጆታ በተጨማሪም ያስከተለው የዓለም የነዳጅ ዋጋ ግሽበት በአፍሪካ ሀገራትም የናፍጣ እና የቤንዚን መሸጫ ዋጋ ከፍ እንዲል አድርጎታል።
የምግብ ዋጋ መናር እና ዝቅተኛ የኢኮኖሚ እድገት በአፍሪካ አህጉርን ጨምሮ በዓለም ዙሪያ በሚገኙ ደሃ ሀገራት ውስጥ የሚገኙ በሚሊየን የሚቆጠሩ ሰዎችን አደጋ ውስጥ እንደጣለም ይነገራል።