ፖለቲካ
በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ኮንጎ በተፈጸመ የሚሊሻ ጥቃት 60 ሰዎች ተገደሉ
ኢቱሪ በተባለው የሃገሪቱ አካባቢ የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ናቸው ጥቃቱን የፈጸሙት ተብሏል
ጥቃቱ በተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ የተፈጸመ ነው
በምስራቃዊ ዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ በሚገኝ አንድ የተፈናቃዮች መጠለያ ጣቢያ በተፈጸመ የሚሊሻ ጥቃት በትንሹ 60 ሰዎች ተገድለዋል ተባለ፡፡
ጥቃቱ ኢቱሪ በተባለው የሃገሪቱ አካባቢ በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ዛሬ ረቡዕ ጠዋት የተፈጸመ ነው ተብሏል፡፡
የCODECO ታጣቂዎች የጥቃቱ ፈጻሚ መሆናቸውንም ሮይተርስ የመጠለያ ጣቢያው የሰብዓዊ አስተባባሪዎችን ዋቢ አድርጎ ዘግቧል፡፡
ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በርካታ የኢቱሪ አካባቢ ነዋሪዎችን የገደሉት ታጣቂዎቹ በርካቶችን ማፈናቀላቸውን የተመድ መረጃዎች ያመለክታሉ፡፡
በመጠለያ ጣቢያው እስካሳለፍነው ታህሳስ ድረስ 4000 የሚደርሱ ተፈናቃዮች ይኖሩ እንደነበርም መረጃዎቹ አመልክተዋል፡፡
አሁንም በተፈናቃዮች ላይ በፈጸሙት ጥቃት በትንሹ 60 ሰዎች መገደላቸውና በርካቶች መጎዳታቸውም ነው የተነገረው፡፡
ሆኖም የሃገሪቱ መንግስት ጥቃቱን በተመለከተ እስካሁን ያስታወቀው ነገር የለም፡፡