የፀጥታው ምክር ቤት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውን “የተመድ የሰላም ማስከበር ተልዕኮ” አራዘመ
ሁሉም የታጠቁ ቡድኖች ሁሉንም አይነት “ሁከት እና አለመረጋጋትን ከመፍጠር እንዲታቀቡ” ምክር ቤቱ ጠይቋል
ምክር ቤቱ ፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ በፖለቲካው መስክ እያደረጉት ያለውን ጥረትም አድንቋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት(ተመድ) የፀጥታው ምክር ቤት በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የሚገኘውን የተመድ ሰላም ማስከበር ተልዕኮን እስከ ፈረንጆቹ ታህሣሥ 20 ቀን 2022 ድረስ ለተጨማሪ አንድ ዓመት እንዲራዘም የቀረበውን የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምፅ አጸደቀ።
በውሳኔ ቁጥር 2612 መሰረት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የማረጋጋት ተልዕኮ በዲ.አር ኮንጎ/MONUSCO / በመባል የሚታወቀውን ሰላም አስከባሪ ለተልእኮው የተፈቀደውን የሰራዊት ጣሪያ በትንሹ ከ14,000 ወደ 13,500 ለመቀነስ ወስኗልም ነው የተባለው፡፡
እንደ ሲጂቲኤን ዘገባ ፡እስከ 360 የሚደርሱ የፖሊስ አካላት በጊዜያዊነት እንዲሰማሩም ተፈቅዷል። .
የውሳኔ ሃሳቡ የተባበሩት መንግስታት ሴክሬታሪያትን በሚገባ በመሬቱ ላይ ያለውን አውንታዊ ለውጥ ላይ በመመርኮዝ የ MONUSCO ወታደራዊ ስምሪት ደረጃና መጠን በሂደት እንዲቀንስ እንደሚደረግም የሚያመላክት ነው ተብሏል፡፡
የፕሬዚዳንት ፌሊክስ ቲሺሴኪዲ በፖለቲካዊው መስክ እና ሰብአዊ መብቶች ጉዳይ ላይ እያደረጉት ያለውን ጥረት በደስታ እንደሚቀበል ያስታወቀው ምክር ቤቱ፤ሁሉም የታጠቁ ቡድኖች ሁሉንም አይነት ሁከት እና አለመረጋጋትን የሚፈጥሩ እንቅስቃሴዎችን በአስቸኳይ እንዲያቆሙም ጠይቋል።
ምክር ቤቱ በሰብአዊ እና በህክምና ሰራተኞች ላይ እየጨመረ የሚሄደው ጥቃቶች እንዲሁም በምስራቃዊው የሀገሪቱ ክፍል የሰብአዊ አገልግሎት አቅርቦት ላይ እንቅፋት የፈጠረበት ሁኔታ አሳሳቢ መሆኑን ገልጿል፡፡
ሁሉም አካላት ሙሉ ፣ደህንነቱ የተጠበቀ ፣አፋጣኝ እና ያልተገደበ ሰብአዊ ተደራሽነት እንዲፈቅዱ እና እንዲያመቻቹ አሳስቧል።
ምክር ቤቱ ተመድ የማረጋጋት ተልዕኮ በዶር ኮንጎ/MONUSCO / ስትራቴጂያዊና ቅድሚያ የሚሰጣቸው ጉዳዮች ሲቪሎችን መጠበቅ፣ የዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ የመንግስት ተቋማትን ማረጋጋትና ማጠናከር፣ ቁልፍ የአስተዳደር እና የጸጥታ ማሻሻያዎችን መደገፍ እንዲሆንም ወስኗል፡፡