እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 73 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ
የፍልስጤም ባለስልጣናት ስልክ እና ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክያት የነፍስ አድን ሰራው ተስተጓጉሏል ብለዋል
የእስራኤል -ሀማስ ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን በጦርነቱ እስካሁን ከ42ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል
እስራኤል በጋዛ በፈጸመችው ጥቃት ቢያንስ 73 ሰዎች መገደላቸው ተገለጸ።
እስራኤል በሰሜን ጋዛ ቤት ላሂያ በሚገኙ በርካታ ቤቶች እና የመኖሪያ ህንጻዎች ላይ ባደረሰችው ጥቃት በርዘን ሚቆጠሩ ሰዎች መገደላቸውን ሮይተርስ የዶክተሮችን እና የጤና ባለሙያዎችን ጠቅሶ ዘግቧል።
የሀማስ የሚዲያ ቢሮ ቢያንስ 73 ሰዎች መገደላቸውን ገልጿል።
ከጤና ሚኒስቴሩ የተገኘ ይፋዊ ቁጥር ባይኖርም፣ ሜድዋይ አባስ የተባሉት ከፍተኛ የጤና ሚኒስቴሩ ባለሙያ ቁጥሩ ትክክል ነው ብለዋል።
የእስራኤል ጦር ክስተቱን እየመረመርኩት ነው፤ ነገርግን በሀማስ የቀረበው የተጎጅዎች ቁጥር የተተጋነነ ነው ብሏል። ጦሩ የቀረበው ቁጥር ካለው መረጃ ጋር እንደማይጣጣም እና የተጠቀመው መሳሪያ በትክክል በሀማስ ኢላማ ላይ ያነጣጠረ ነበር ብሏል።
የፍልስጤም ባለስልጣናት ስልክ እና ኢንተርኔት በመቋረጡ ምክያት የነፍስ አድን ሰራው ተስተጓጉሏል ብለዋል። የፍልስጤም የጤና ሚኒስቴር ቀደም ብሎ በጥቃቱ 35 ሰዎች በእስራኤል ጥቃት ተገድለዋል ብሏል።
"ይህ የዘር ማጥፋት እና የማጽዳት ወንጀል ነው። ወራሪ ኃይሉ በቤይት ላሂያ ዘግናኝ ወንጀል ፈጽሟል" ብሏል የሀማስ ሚዲያ ቢሮ።
ሮይተርሰ ነዋሪዎችን እና የጤና ባለሙያዎችን ጠቅሶ እንደዘገበው ከሆነ የእስራኤል ጦር በጋዛ በሚገኘው ትልቁ የጃባሊያ የስደተኞች ካምፕ ላይ በቅርብ ባሉት የቤት ሀኖን እና ቤይት ላሂያ ከተሞች ታንክ በማስጠጋት ጭምር ከበባ እያጠናከረች ነው።
የእስራኤል ጦር በጃባሊያ ያሉ ነዋሪዎች ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ ሰጥተዋል። እስራኤል ነዋሪዎች ቦታውን ለቀው እንዲወጡ ማስጠንቀቂያ የምትሰጠው የሀማስ ታጣቂዎችን ለይቶ ለመምታት በማሰብ ነው።
ነዋሪዎች እና የጤና ባለሙያዎች እንደሚገልጹት ከሆነ የእስራኤል ኃይሎች መኖሪያ ቤቶችን በመደብደብ እና ሆስፒታሉን በመክበብ የምግብ እና የመድሃኒት አግልግሎት እንዳይገባ በመከልከል ካምፑን ለቀው እንዲሄዱ እያስገደዱ ይገኛሉ።
ነገርግን የጤና ባለሙያዎች በእስራኤል ጦር ሆስፒታሉን ወይም ህመምተኞችን ጥለው እንዲወጡ ያስላለፈውን ውሳኔ ለመቀበል ፍቃደኛ አልሆኑም።
ቅዳሜ ጠዋት የእስራኤል የጦር አውሮፕላኖች የሟቹን የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋርን አስከሬን የሚየሳዩ በራሪ ወረቀቶችን "ሀማስ ከዚህ በኋላ ጋዛን አይመራም" ከሚል መልእክት ጋር ደቡባዊ ጋዛ በመበተን የጠቅላይ ሚኒሴቴር ኔታንያሁን ንግግር አስተጋብተዋል።
በአብረብኛ የተጻፈው በራሪ ወረቀቱ "መሳሪያ ያስቀመጠ እና ታጋቾችን ያስረከበ በሰላም እንዲኖር ይፈቀድለታል" እንደሚል የደቡባዊ ጋዛ ካን ዮኒስ ነዋሪዎች ተናግረዋል።
የበራሪ ወረቀቱ መልእክት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሲንዋር በራፋ በሚንቀሳቀሱ የእስራኤል ጦር አባላት መገደሉን ተከትሎ ከሰጡት መግለጫ የተወሰደ ነው ተብሏል።
ሲንዋር ባለፈው ጥቅምት ወር ሀማስ በእስራኤል ላይ ካደረሰው ከባድ ጥቃት ጀርባ እንዳለ እስራኤል ታምናለች።
የእስራኤል -ሀማስ ጦርነት እንደቀጠለ ሲሆን በጦርነቱ እስካሁን ከ42ሺ በላይ ፍልስጤማውያን ተገድለዋል ተብሏል።