በእስራኤል የተገደሉት ያህያ ሲንዋር ከ2 ወር በፊት ነበር ኢስማኤል ሀኒየን በመተካት የሃማስ መሪ የሆኑት
የያህያ ሲንዋርን ግድያን ተከትሎ በጋዛ እየተካሄደ ያለው ጦርነት እጣ ፈንታ እና ቀጣዩ የሃማስ መሪ ማን ሊሆን ይችላል የሚለው በበርካቶች ዘንድ ጥያቄን ፈጥሯል።
የሃማስ መሪ ያህያስ ሲንዋር ባሳለፍነው ሐሙስ በደቡባዊ ጋዛ ውስጥ በተደረገ ኦፕሬሽን መገደላቸውን የእስራኤል ጦር አስታውቋል።
የ61 ዓመቱ የሃማስ መሪ ያህያ ሲንዋር በጋዛ ውስጥ የእስራኤል ጦር ጋር እየተዋጋ መገደሉን የሚያሳዩ ምስሎችም ወጥተዋል።
ያህያ ስንዋር የቀድሞውን የሀማሱን ከፍተኛ መሪ ኢስማኤል ሀኒያን በኢራን ዋና ከተማ ቴህራን መገደልን ተከትሎ ነበር ሃማስን እንዲመሩ የተሰየሙት።
የሃማስን ወታደራዊ ክንፍ ሲመሩ የቆዩት ያህያ ሲንዋር፤ ኢስማኤል ሃየን በመተካት ቡድኑን መምራት ከጀመሩ በሁለተኛው ወራቸው ተገድለዋል።
ቀጣዩ የሃማስ መሪ ማን ልሆን ይችላል?
የያህያ ሲንዋርን ግድያን ተከትሎ ቀጥሎ የተዘረዘሩት እጩዎች ቀጣዩ የሃማስ መሪ ሊሆኑ ይችላሉ ተብለው ከተገመቱት ውስጥ ናቸው።
መሃሙድ አል-ዛሃር
መሃሙድ አል-ዛሃር የሃማስ መስራች እና ነባር አባል ሲሆን፤ ወግ አጥባቂ ከሚባሉ ሰዎች መካከል የሚመደብ ነው።
በፈረንጆቹ በ2006 የፍልስጤም የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት አባል ሆኖ መመረጡ የሚታወቅ ሲሆን፤ የሃማስ የመጀመሪያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሆኖ ተሹሞ ነበር።
መሃሙድ አል-ዛሃር በፈረንጆቹ በ1992 እና በ2003 ከሁለት የእስራኤል የግድያ ሙከራዎች ማምለጥ ችሏል።
መሃድ ሲንዋር
ከሰሞኑ የተገደለው የሃማስ መሪ ያያህ ሲንዋር ወንድም የሆነው መሃመድ ሲንዋር ቀጣዩ የሃማስ መሪ ሊሆን ይችላል በሚል ከፍተኛ ግምት ካገኙ ሰዎች መካከል ቀዳሚው ነው።
የያህያ ሲንዋር ወንድም የሆነው መሀመድ ሲንዋር በጋዛ ከእስራኤል ጋር የሚደረገውን ውግያ በማስተባበር እና በመምራት ከፍተኛ ሚና እንደሚኖረው ይጠበቃል፡፡
ሙሳ አቡ-መርዙክ
ሙሳ አቡ-መርዙክ ወደ ሃማስ የተቀየረውን የሙስሊም ወንድማማች የፍሊስጤም ቅርንጫፍ በመመስረት በኩል ትልቁን ሚና የተጫወተ ሰው ነው።
በፈረንጆቹ በ1990ዎቹ ውስጥ የሃማስን የፖለቲካ ቢሮ የመራ ሲሆን፤ እስራኤል የሽብር ጥቃቶችን በማቀናር እና በማገዝ ትከሰዋለች።
መሃመድ ደኢፍ
መሃመድ ደኢፍ በህይወት መኖሩ እስካሁን በይፋ የተረጋገጠ ነገር የለም። እስራኤል በ2024 መጀመሪያ አካባቢ በአየር ድብደባ ገድዬዋለሁ ያለች ሲሆን፤ አንድ የሃማስ ከፍተኛ ባለስልጣን ባሳለፍነው ነሃሴ ወር ላይ ደኢፍ በህይወት ስለመኖሩ ለኤ.ፒ ተናግርዋል።
መሃመድ ደኢፍ የሃማስ መስራች አባል ሲሆን፤ከፈረንጆቹ 2002 ጀምሮ የሃማስ ወታራዊ ክንፍ የሆነውን አል ዲን አልቃሲም ብርዴድን ሲመራ ቆይቷል።
ደኢፍ የጥቅምት 7 ጥቃት ከያህያ ሲንዋር ጋር በመሆን ካቀነባበሩት ሰዎች መካከል እንደሆነ እስራኤል የሚነገር ሲሆን፤ ሃማስ ካለው ጠንከር ያሉ አመራሮች መካከልም ነው የሚመደበው።
ከሃሊል አል-ሃያ
ካሊል አል-ሀያ በኳታር የሚገኝ የሃማስ የፖለቲካ ቢሮ አባል ሲሆን፤ በዶሃ በተደረጉት የተኩስ አቁም ውይይቶች ላይ መሪ ተደራዳሪ ነበር። በአሁኑ ጊዜ ኑሮውን በኳታር አድርጓል።
የአሜሪካ ባለስልጣን ለሲኤንኤን እንደተናገሩት አል-ሀያ በተኩስ አቁም ንግግሮች ውስጥ በተጫወተው ሚና “ምናልባት አሜሪካ ቀጣይ የሃማስ መሪ እንዲሆን የምትፈልገው ሰው ነው” ብለዋል።
የሃስ አመራር የሆኑት ከሃሊል አል-ሃያ በፈረንጆቹ በ2007 በዛጋ ውስጥ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው ላይ በተፈጸመ ጥቃት ለጥቂት ከሞት ያመለጡ ሲሆን፤ የቤተሰቦቻውን አባለት ግን በጥቃቱ አጥተዋል።
ካሊድ ማሻል
ከሊድ መሻ ከፈረንጆቹ 2006 ጀምሮ የሃማስ ጠቅላይ መሪ የነበረ ሲሆን፤ የሃማስ የቀድሞ የፖለቲካ ቢሮ መሪም እንደነበረ ይነገራል።
በአሁኑ ወቅት ኑሮውን በኳታር ያደረገው ማሻል በ1990ዎቹ መጨረሻ ለይ ከተቃጣበት የግድያ ሙከራ ማምለጡምአይዘነጋም።
የ68 ዓመቱ ማሻል በቅርቡ ከሮይተርስ ጋር ባደረገው ቆይታ፤ ሃማስ በእስራኤል ድብደባ ከፍተኛ ጉዳት ቢያስተናግድም “እንደ ፊኒክስ ወፍ ነፍስ ዘርቶ ይነሳል” ማለታቸው ይታወሳል።
“ሰማዕታት እና ወታደራዊ አቅማችን የሚያሳጡ በርካታ ምዕራፎችን አልፈናል፤ ይሁን እንጂ በነዚህ ሂደቶች ሁሉ የፍልስጤማውያን የተጋድሎ መንፈስና ለሞት አይበገሬነት እንደ ፊኒክስ ወፍ እየሆነ ቀጥሏል” ሲሉም ተናግረዋል።