የእስራኤል አውሮፕላኖች የያህያ ሲንዋር አስክሬን ፎቶን የሚያሳይ በራሪ ወረቀት በጋዛ በተኑ
አውሮፕላኖቹ በራሪ ወረቀቶቹን ሲበትኑ እና የታጻፈባቸውን መልእክቶች የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት እየተዘዋወሩ ነው
በደቡባዊ ጋዛ ከተበተነው የአስክሬን ፎቶ በተጨማሪ “ሃማስ ከዚህ በኋላ ጋዛን አያስተዳድርም” የሚል መልዕክት የተጻፈባቸው ወረቀቶችም ተሰራጭተዋል
የእስራኤል አውሮፕላኖች ከሰሞኑ የተገደለውን የሀማስ መሪ ያህያ ሲንዋር አስክሬን ፎቶን የሚያሳዩ በራሪ ወረቀቶችን በተኑ፡፡
“ሀማስ ከእንግዲህ ጋዛን አይገዛም” የሚል መልዕክት የያዘ ጽሁፍ የታጻፈባቸው በራሪ ወረቀቶች የያህ ሲንዋርን ሞት ተከትሎ የእስራኤሉ ጠቅላይ ሚኒስትር ቤንያሚን ኔታንያሁ የተጠቀሙበትን ቋንቋ አስተጋብቷል።
በአረበኛ ቋንቋ ተጽፎ በደቡብ ካን ዮኑስ እና በሌሎች አካባቢዎቸ የተሰራጨው በራሪ ወረቀት “መሳሪያውን ጥሎ ታጋቾቹን የሚያስረክብ ማንም ሰው በሰላም እንዲኖር ይፈቀድለታል” የሚል ጽሁፍ ታክሎበታል።
አውሮፕላኖቹ በራሪ ወረቀቶቹን ሲበትኑ እና የታጻፈባቸውን መልእክቶች የሚያሳዩ ተንቀሳቃሽ ምስሎች በማህበራዊ ትስስር ገጾች ላይ በስፋት እየተሰራጩ ነው።
በራሪ ወረቀቶቹ የተበተኑት በሰሜናዊ ጋዛ በተጠናከረው ውግያ 32 ሰዎች መገደላቸው ከተሰማ እና በሰሜን ጃባሊያ በሚገኙ ሆስፒታሎች ዙሪያ የእስራኤል ጦር ከበባውን ስለማጠናከሩ የፍልስጤም የጤና ባለስልጣናት እየተናገሩ በሚገኙበት ወቅት ነው።
ከሀሙስ ጀምሮ በሰሜናዊ ጋዛ በታንክ ፣ በእግረኛ እና በአየር ሀይል ተጠናክረው በቀጠሉት ውግያዎች እስካሁን ከ33 በላይ ሰዎች ሲገደሉ በመላው ጋዛ የሞተው አጠቃላይ ሰው ቁጥር ደግሞ ከ72 ተሸግሯል።
ምንም አይነት የመቀዛቀዝ ምልክት ያልታየበት አንድ አመት ባስቆጠረው የጋዛ ጦርነት ከ42,500 በላይ ፍልስጤማውያንን የገደለ ሲሆን ሌሎች ከሟቾች ጋር ያልተቆጠሩ 10,000 የሚጠጉ ሰዎች በፍርስራሾች ውስጥ ሞተው እንደሚገኙ የጋዛ የጤና ባለስልጣናት ይገልጻሉ።
ከዚህ ባለፈም በተደጋጋሚ በሚፈጸሙ የአየር ጥቃቶች ጉዳት የሚደርስባቸው እና የሚሞቱ ሰዎች ቁጥር መጨመር በአካባቢው የሚገኙ ሆስፒታሎች ማስተናገድ ከሚችሉት አቅም በላይ እንዲጨናነቁ አድርጓል ብለዋል።
ባለስልጣናቱ የእስራኤል ጦር ታጣቂዎችን ከንጹሀን ሳይለይ እየገደለ እንደሚገኝ ሲወቅሱ፤ ቴልአቪቭ በበኩሏ ንጹሀን ጥቃት የሚፈጸምባቸውን ስፍራዎች ለቀው እንዲወጡ የሚነገሩ ተደጋጋሚ ማስጠንቀቂያዎች የሃማስ ተዋጊዎችን ከሲቪሎች ለመለየት ያለሙ ስለመሆናቸው ትከራከራለች።
በተጨማሪም ሲቪሎችን ከጃባሊያ ወይም ከሌሎች ሰሜናዊ አካባቢዎች ለማፅዳት ምንም አይነት ስልታዊ እቅድ እንደሌለ አስተባብላለች።
የእስራኤል ጦር በአካባቢው የሚንቀሳቀሱት ወታደሮች በሲቪሎች እና በህክምና መሰረተ ልማቶች ላይ የሚደርሰውን ጉዳት የመቀነስ አስፈላጊነት ላይ መመሪያ እንደተሰጣቸውም ነው የተናገረው።