የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ሁለት የአግሪ ፊን ሽልማቶችን አሸነፈ
ኤጀንሲው በዘረጋው የነጻ መረጃ ስርዓት 48 ሚሊዮን አርሶ አደሮች የግብርና መረጃዎች ሰጥቻለሁ ብሏል
ተቋሙ ሽልማቱን ያሸነፈው የአንበጣ መንጋ እና ሌሎች ለግብርና ስራዎች ፈተና የሆኑ ችግሮችን ለመፍታት ባደረገው ጥረት ነው
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ (ኤቲኤ) ሁለትየአግሪ ፊን ሽልማቶችን ማሸነፉን አስታወቀ፡፡
ኤቲኤ ሽልማቶቹን ያሸነፈው “ዲጂታል መረጃን በመጠቀም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ማገልገል” እና “አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ በመንግስት እና በግሉ ዘርፍ በአጋርነት የሚሰሩ ፈር ቀዳጅ ሥራዎች” በሚሉት ሁለት ምድቦች መሆኑን ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ አስታውቋል።
“ዲጂታል መረጃን በመጠቀም አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ማገልገል” በተሰኘው በመጀመሪያው ምድብ ስር ኤጀንሲው ከዳልበርግ እና ከመርሲ ኮር አግሪፊን ቡድኖች ጋር በመተባበር የመረጃ ምንጮችን በሙሉ በመረጃ ቋቱ ውስጥ በአንድ ቦታ የሚያሰባስብ የመረጃ ቋት ለመፍጠር ችሏል።
ይህን ማድረጉ ከሰባት የተለያዩ ፕሮጀክቶች የሚገኙ መረጃዎችን ተንትኖ ለመጠቀም እና ውሳኔ ለመስጠት አስችሎታል።
2 ነጥብ 5 ሚሊዮን አርሶ አደሮችን ያቀፉትን የግብርና ኮሜርሻላይዜሽን ክላስተሮች ለመደገፍ እንዳስቻለውም ነው ያስታወቀው፡፡
በዝርዝር የተዘጋጁ የአርሶ አደር ፖሊሲዎችን ለመቅረጽ ከማገዝም በላይ ለመንግስት እና ለግል ተቋማት የሚያገለግል ሀብት ነውም ብሏል።
የኤጀንሲው ዋና ሥራ አስፈጻሚ ማንደፍሮ ንጉሴ (ዶ/ር) “ሽልማቱ ልናገለግላቸው የምንተጋላቸውን አነስተኛ ይዞታ ያላቸው አርሶ አደሮችን ለማገዝ ለምንሠራቸው ሥራዎች ዕውቅና የሚሰጥ መሆኑ መነሳሳትን ይፈጥራል” ብለዋል።
ሁለተኛው ሽልማት ደግሞ ኤጀንሲው አርሶ አደሮች በ8028 ነጻ የስልክ መስመር የበረሀ አንበጣ መከላከል መረጃዎች እና ሌሎች አስፈላጊ የሆኑ የግብርና ስራ መረጃዎችን ለአርሶ አደሩ በማድረሱ እንደሆነም ተገልጿል።
8028 ከሰባት ዓመት በፊት በአራት ክልሎች ተግባራዊ መደረግ የጀመረ ሲሆን በአሁኑ ወቅት በ210 የስልክ መሥመሮች ላይ በመስራት ላይ ይገኛል።
አሁን ላይ ይህ ነጻ የአርሶ አደሮች መስመር በአምስት ቋንቋዎች አገልግሎት በመስጠት ላይ ሲሆን እስካሁን 48 ሚሊዮን አርሶ አደሮች ተደዋውለውበታል ተብሏል።
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ በ2002 ዓ.ም የተቋቋመ ሲሆን ዘመናዊ ግብርና ማስፋፋትን ዓላማው ያደረገ መንግስታዊ ተቋም ነው።