በኢትዮጵያ በዚህ ዓመት የአንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የሚያስችል ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የግብርና ሚኒስቴር ገለፀ
በኢትዮጵያ እና በአጎራባች ሀገራት የድርቁ ጊዜ ረዘም ማለቱ የበረሃ አንበጣ እንዳይራባ ማድረጉ ተገልጿል
ሚኒስቴሩ አውሮፕላኖችን በመጠቀም አንበጣ ባይኖርም ቅኝት በማድረግ የቁጥጥር ስራዎችን እየሰራ መሆኑን አስታውቋል
በኢትዮጵያ አንበጣ መንጋ እንዳይከሰት የቅድመ ጥንቃቄ ስራዎች እየተሰሩ እንደሚገኙ የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋትጥበቃ ዳይሬክተር አቶ በላይነህ ንጉሴ ለአል ዐይን አማረኛ እንደተናገሩት፥ አሁን ላይ ከበረሃ አንበጣ ጋር ተያይዞ ያለው ሁኔታ እየተረጋጋ ነው።
አቶ በላይነህ አክለውም ባለፈው ዓመት የነበረው የበረሃ አንበጣ ሁኔታ “በአሁኑ በእርግጠኝነት አይደገምም፤ ለዚህም ብዙ ምክንያቶች አሉ” ብለዋል።
ከእነዚህም የአየር ሁኔታው፡ ማለትም የድርቁ ጊዜ ረዘም ማለት አንዱ መሆኑን ያነሱት አቶ በላይነህ፣ ምክንያቱ ደግሞ “አንበጣ እንቁላ ለመጣል እርጥበት ያስፈልገዋል፤ በድርቁ ምክንያት እርጥበት ማግኘት ስላልቻለ የመራባቱን መጠን በእጅጉ ቀንሶታል” ብለዋል።
ስለዚህም አንበጣው የእድገት ጊዜውን ለመጨረስ እና እንቁላል መጣል የሚጀመርበት ደረጃ ላይ አይደለም ሲሉም ተናገረዋል።
በጎረቤት ሀገራት ያለውን ሁኔታ በተመለከትም፣ በአብዛኛው በጎረቤት ሀገራት ያለው ሁኔታ ከሀገር ውስጥ ጋር ተመሳሳይ በመሆኑ ከውጭ ገብቶ ጉዳት ያደርሳል የሚል ስጋት እንደሌለም አስታውቀዋል።
ነገር ግን በፑንትላንድ እና ቀይ ባህር አካባቢ መጠነኛ መራባቶች መኖራቸውን ያነሱት አቶ በላይነህ፤ ሚኒስቴሩ ካለው ዝግጁነትና ኃይል ጋር ሲነጻጸር መቆጣጠር የሚያስችል ሙሉ አቅም እንዳለው ነው የገለጹት።
ሀገር ውስጥም ቢሆን ዝናብ ቢጥል እና የመራባት አቅም ቢኖረውም ሚኒስቴሩ ካለው አቅም አንጻር “በቂ ዝግጅት ስለተደረገ መቆጣጠር ይቻላል” ብለዋል።
በአሁኑ ወቅት የግብርና ሚኒስቴር አንበጣ መቆጣጠሪያ አውሮፕላኖችን በመጠቀም ፣ አንበጣ ባይኖርም ቅኝት በማድረግ ለቁጥጥር የሚያስችል ዝግጅት እያደረገ መሆኑንም አቶ በላይነህ አንስተዋል።
ባለፈው ጊዜ ተራብቶ የነበረ እንበጣ አሁን ላይ በማደግ ላይ በመሆኑ በተለይም በባሌ እና በምስራቅ ሀረርጌ አካባቢዎች ላይ የተበታተኑ ካሉ በሚል የቁጥጥር ስራ እየተሰራ መሆኑንም አስታውቀዋል።
ባለፉት ጊዜያት ከተከሰተው የአንበጣ መንጋ ጋር በተያያዘ ጥናት መደረጉን በመጠቆም ፣ በጥናቱ ላይ በመመስረት ለአርሶ አደሩ ድጋፍ እንደሚደረግም ገልጸዋል።
በዚህም በአንበጣ መንጋ ጉዳት ለደረሰባቸው አርሶ አደሮች ፣ የደረሰባቸውን ጉዳት ለማካካስ ለቀጣዩ ክረምት የዘር፣ የማዳበሪያ እና ሌሎች ድጋፎች አእንደሚደረግላቸው ነው የእፅዋትጥበቃ ዳይሬክተሩ አቶ በላይነህ የተናገሩት።
ባለፈው ዓመት በኢትዮጵያ የተለያዩ አካባቢዎች በብዛት ተከስቶ ለረዥም ጊዜ የቆየው የበረሃ አንበጣ መንጋ ፣ ከፍተኛ ሰብል በማውደም በምርትና ምርታማነት ላይ ጉልህ ጉዳት ማድረሱ ይታወሳል፡፡ በዚህም ሳቢያ በርካታ አርሶአደሮች ለተረጂነት ተጋልጠዋል፡፡