የአንበጣ መንጋ “ስርጭቱ እየጨመረ ነው፤ ወደፊትም ይጨምራል”፡ ግብርና ሚኒስቴር
“ሁኔታው ተጠናክሯል፤ በየመን ያለው ተሻግሮ ሊመጣ ይችላል” - በሚኒስቴሩ የእፅዋት ጤናና ጥራት ዳሬክተር ወልደሀዋሪያት
በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ እየተፈለፈለ ስለሆነ የአንበጣ መንጋው እንደሚጨምር ግብርና ሚኒስቴር ስጋቱን ገልጿል
በአሁኑ ወቅት የበረሃ አንበጣ እየተፈለፈለ ስለሆነ የአንበጣ መንጋው እንደሚጨምር ግብርና ሚኒስቴር ስጋቱን ገልጿል
በሰኔ ወር 2011ዓ.ም በኢትዮጵያ የተከሰተው የበረሃ አንበጣ መንጋ የስርጭት አድማሱን አስፍቶ አሁን ላይ 175 የሚሆኑ ወረዳዎች ማዳረሱን የግብርና ሚኒስቴር አስታውቋል፡፡
ከሁለት ወር በፊት የበረሃ አንጣው በተለያዩ ክልሎች የሚገኙ 160 ወረዳዎች ላይ መከሰቱን የግብርና ሚኒስትር ዲኤታው ካባ ኡርጌሳ (ዶ/ር) ገልጸው ነበር፡፡ ሚኒስትር ዲኤታው የበረሃ አንበጣው ከዚህ በፊት ከሚከሰትበት የምስራቅ ኢትዮጵያ ክፍል አልፎ ባልተለመደ ሁኔታ አሁን ወደ ምእራብ ኢትዮጵያ መዛመቱን መናገራቸው ይታወሳል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የእፅዋት ጤናና ጥራት ዳሬክተር ጄነራል ወልደሀዋሪያት አሰፋ ለአል-አይን አማርኛ እንደገለጹት እስካሁን የበረሀ አንበጣው 300ሺ95 ሄክታር ላይ የተከሰተ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 300ሺ 40 ሄክታር ያካለለ የመከላከል ስራ ተስቷል፡፡
አቶ ወልደሀዋሪያት አንደገለጹት መንግሰት እስካሁን በ593ሺ ሄክታር ላይ ዳሰሳ አድርጓል፡፡
በሰው ሃይልና በአውሮፕላን የመከላከል ስራ እየተሰራ እንደሆነ የገለጹት ዳይሬክተሩ እስካሁን 95 በመቶ የመከላከል ስራ ተሰርቷል ብለዋል፡፡ ዳይሬክተሩ እንደገለጹት የመከላከል ስራው የተሰራው በስድስት አውሮፕላን፤ ኬሚካል በሚረጩ መኪናዎችና በሰው ሃይል ነው፡፡
ምንም እንኳን የበረሃ አንበጣው የተከሰተበት ቦታ ወደ 175 ወረዳዎች ከፍ ቢልም “ተከሰተ ማለት ጉዳት አደረሰ ማለት አይደለም” ብለዋል አቶ ወለድሀዋሪያት፡፡
የበረሀ አንበጣው ያስከተለውን ጉዳት ለመገምገም ጥናት እየተካሄደ ነው፤ጥናቱ ሲጠናቀቅ ያስከተለውን ጉዳት በአሀዝ መግለጽ እንደሚቻል ዳይሬክተሩ ጠቅሰዋል፡፡
በኢትዮጵያ የበረሃ አንበጣ መፈልፈያ ቦታዎች
በአሁኑ ሰአት በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች የበረሃ አንበጣ እየተፈለፈለ ስለሆነ ስርጭቱ እንደሚጨምር ዳሬክተሩ ወልደሀዋሪያት ተናግረዋል፡፡
“ስርጭቱ እየጨመረ ነው፤ ውደፊትም ይጨምራል፤ ትንበያው እንደሚመለክተው ይጨምራል፡፡ በድሬደዋ፣በሰሜን አፋር አንበጣ እየተፈለፈለ ነው፤ በደቡብ ኦሮሚያም ጉጂና ቦረናም እየተፈለፈለ” መሆኑን አቶ ወልደ ሀዋሪያት ገልጸዋል
በደቡብ ክልል በደቡብ ኦሞም እየተፈለፈለ መሆኑን ዳሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
አሁን ያለው የአየር ሁኔታ ለአንበጣ መራባት ምቹ ሁኔታ በመፍጠሩ አንበጣ እየተፈለፈለ አንደሚገኝ ዳይሬክተሩ ገልጸዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ጎረቤት ሶማሊያና ከኬንያ በመምጣት በደቡብ ኦሮሚያና በደቡብ ክልል እየተስፋፋ ነው ያሉት ዳሬክተሩ “ሁኔታው ተጠናክሯል፤ በየመን ያለው ተሻግሮ ሊመጣ ይችላል” ብለዋል፡፡
ችግሩ “የከፍ ሊሆን አንደሚችል” በማሰብ የግብርና ሚኒስቴር አንበጣ መንጋውን ለመከላከል በቂ ዝግጅት አድርጓል ብለዋል አቶ ወለደሀዋሪያት፡፡
አንበጣ ለመከላከል እስከሁን የወጣው ወጭ ምን ያህል ነው?
እንደ አቶ ወልደሀዋሪያት ከሆነ እስካሁን መንግስት 200 ሚሊዮን ብር ለአንበጣ መከላከል አውሏል፡፡ መንግስት ከውጭ አጋር ድርጅቶችም እርዳታ በተለያየ መልኩ አግኝቷል፡፡፡ የአለም የምግብ ድርጅት (ፋኦ) የአንበጣ ለመከላከል የሚውል አውሮፕላን ኪራይ በመክፈል ለመከላከል ስራ እንዲሰማሩ አድርጓል፡፡
የአለም ባንክ ለአንበጣ መከላከል፣ የመዳበሪያ ግብአት አቅርቦትና ለአስቸኳይ የምግብ እርዳታ የሚውል የ63 ሚሊዮን ዶላር ለኢትዮጵያ መንግስት መስጠቱን በድረ-ገጹ ከሁለት ሳምንት በፊት አስታውቋል፡፡ ኢትዮጵያ ያገኘችው 63 ሚሊዮን ዶላር የአለም ባንክ ለአንበጣ መከላከልና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ከመደበው 500 ሚሊዮን ዶላር በመቀነስ ነው፤ በዚህ እርዳታ መርሀግብር ብዙ የምስራቅ አፍሪካ ሀገራት ተጠቃሚ ሆነዋል፡፡የተገኘውን እርዳታ ለመውሰድ ስምምነት መፈረሙን ዳሬክተሩ አቶ ወልደሀዋሪያት አረጋግጠዋል፡፡
የኮሮና ቫይረስ መከሰት የበረሀ አንበጣን በከለከላከል ላይ “የተወሰነ ተጽእኖ” እንዳሳደረ ገልጸዋል፡፡
ከ20ና 30 አመት ወዲህ በከፍተኛ መጠን የተከሰተው አንበጣ
ከባለፈው አመት ጀምሮ የተከሰተው የአንበጣ መንጋ ከባለፉት 30 አመታት ወዲህ ታይቶ በማይታወቅ መልኩ በከፍተኛ መጠን መከሰቱን ዳሬክተሩ ወልደሀዋሪያት አስታውቀዋል፡፡
ከዛሬ 50 አመት በፊት በአሁኑ የአማራ፣የትግራይና የኤርትራ በከፍተኛ መጠን ተከስቶ እንደነበር አቶ ወልደሀዋሪያት ገልጸዋል፡፡ እንደ አቶ ወልደሀዋሪያት ገልጻ የአየርንብረት ለውጥ ምክንያት ለአንበጣ መራባት ምቹ ሁኔታ መፈጠሩ ለበረሃ አንበጣ መራባትና መስፋፋት ምክንያት አንደሆነ ይናገራሉ፡፡ ከዚህ በተጨማሪም ለአንበጣ የሚመች ዝናባዊ ሁኔታና በሶማሊያ ያለው የመከላከል የአቅም ማነስ ለአንበጣው መንጋ ምቹ ሁነታ ፈጥሯል ብለዋል አቶ ወልደሀዋሪያት፡፡
የበረሃ አንበጣው በስድስት ክልሎች ማለትም በአማራ፣በትግራይ፣በኦሮሚያ፣በደቡብና በአፋርና በሀረሪ እንዲሁም በድሬደዋ መከሰቱን ተገልጿል፡፡