ግጭቱን ለማስቆም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ አጣዬ ቢገባም መኖሪያ ቤቶች እና ተቋማት መቃጠላቸውን እማኞች ገልጸዋል
በአጣዬ እና አካባቢው አዲስ ግጭት መቀስቀሱ የአካባቢው ነዋሪዎች ገለጹ።
በአማራ ክልል ሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አዋሳኝ አካባቢዎች ላይ ከአራት ቀናት በፊት የተከሰተው ግጭት ተባብሶ መቀጠሉን ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ተናግረዋል።
ለደህንነታቸው በመስጋት ስማቸው እንዳይገለጽ የፈለጉ ነዋሪዎች እንደተናገሩት ከሆነ ባሳለፍነው ቅዳሜ ጥር 13 ቀን 2015 ዓ/ም እሁድ ምሳ ሰዓት ላይ በአካባቢው የሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች በሰሜን ሸዋ ዞን ኤፍራታ እና ግድም ወረዳ ስር ባለችው ጀውሀ ከተማ ለጸጥታ ስራ በተሰማራው የአማራ ልዩ ሀይል ላይ ጥቃት በመክፈታቸው ነበር የመጀመሪያው የጸጥታ ችግር የተፈጠረው።
በዚህ ጥቃት ምክንያት የጀቡሀ አስተዳዳሪን እና የአማራ ልዩ ሀይልን ጨምሮ በድምሩ የ30 ሰዎች ህይወት ማለፉን አስከሬን በማንሳት ስራ ላይ የተሰማራ አንድ የጀቡሀ ከተማ ነዋሪ ነግሮናል።
ይህ ጥቃት እሁድ ዕለት ጋብ ብሎ የነበረ ቢሆንም በትናንትናው ዕለት በጀቡሀ፣ በሰንበቴ፣ ሸዋሮቢት ከተማ አስተዳድር እና ቀወት ወረዳ ስር ወዳሉ ቀበሌዎች መስፋፋቱ ተገልጿል።
ግጭቱን ለመቆጣጠር ተጨማሪ የአማራ ልዩ ሀይል ከአጣዬ አቅጣጫ ወደ ጀቡሀ እና ሸዋሮቢት በመጓዝ ላይ እያለ በኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን የጅሌ ጥሙጋ ወረዳ ዋና ከተማ በሆነችው ሰንበቴ ሲደርሱ ከመንገድ ዳር ባደፈጡ ታጣቂዎች ተኩስ እንደተከፈተባቸውም ስሙ እንዳይጠቀስ የፈለገ የከተማዋ ነዋሪ ለአል ዐይን ተናግራል።
ይሄንን ተከትሎም ግጭቱ ከጀቡሀ አልፎ ወደ ሰንበቴ እና አጣዬ ሊስፋፋ መቻሉን ነዋሪው ገልጿል።
ዛሬ ሌሊትም የሀገር መከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው መግባቱን ተከትሎ ረፋድ ላይ ግጭቱ የረገበ ቢሆንም ከምሳ ሰዓት ጀምሮ ግን ቁጥራቸው ከፍተኛ የሆኑ እና ጦር መሳሪያ የታጠቁ ሰዎች ወደ አጣዬ ከተማ ገብተው ጥቃት መክፈታቸውን አንድ የአጣዬ ከተማ ነዋሪ ገልጸዋል።
እንደ ነዋሪው አስተያየት ከአጣዬ አጎራባች ቀበሌዎች የመጡ ታጣቂዎች የመንግስት ተቋማትን እና የዜጎችን መኖሪያ ቤቶች አቃጥለዋል።
ነዋሪዎቹ እንደተናገሩት በአጣዬ ማረሚያ ቤት የነበሩ እስረኞችን አስፈትተዋል።
በስፍራው ያለው የሀገር መከላከያ ሰራዊት እና ወደ ከተማዋ የገቡት ታጣቂዎች ብዛት የማይመጣጠን በመሆኑ ጥቃቱን ለመቆጣጠር እንዳልቻለም አስተያየት ሰጪው ተናግሯል።
አጣዬ ከተማ ከዚህ በፊት በደረሰባት ተደጋጋሚ ጥቃት ሙሉ ለሙሉ ወድማ የነበረ ቢሆንም ከረድዔት ተቋማት፣ ከአማራ ክልል እና ፌደራል መንግሥት ተቋማት ድጋፍ የመንግስት ተቋማት ወደ አገልግሎት በመመለስ ላይ ነበሩ።
እንዲሁም በተለያዩ ተቋማት ድጋፍ የወደሙ የግለሰብ መኖሪያ ቤቶች መልሰው የተገነቡ ቤቶች በአሁኑ ጥቃት ለአራተኛ ጊዜ መውደማቸው ተገልጿል።
ከተማዋን በተደጋጋሚ እያወደመ ያለው ማን ነው? በሚል ለነዋሪው ላቀረብንላቸው ጥያቄም
"መንግስት እና ሌሎችም ጥቃቱን ኦነግ ሸኔ አደረሰው ይላሉ እውነታው ግን ከከተማዋ የተለያዩ አገልግሎቶችን እያገኙ ያሉ እና አብረውን የሚኖሩ ነዋሪዎች ናቸው፣ እናውቃቸዋለን በተደጋጋሚ ወንጀል እየፈጸሙ ነው ለትንሽ ጊዜ ይታሰሩና በእርቅ እና ሽምግልና ስም ይለቀቃሉ አጥፊዎች ቅጣት ስለማይተላለፍባቸው አሁንም እያቃጠሉ ያሉት እነዚህ ሰዎች ናቸው" ብለዋል።
አሁንም ሳይረፍድ መንግሥት ለአጣዬ እና አካባቢው ትኩረት እንዲሰጥ የጠየቁት እኝህ አስተያየት ሰጪ ተጨማሪ የጸጥታ ሀይል እንዲገባላቸውም ጠይቀዋል።
የሰሜን ሸዋ እና ኦሮሞ ብሄረሰብ ዞኖች እና የአማራ ክልል መንግስት በሁለቱ ዞኖች አዋሳኝ አካባቢዎች ስለተከሰተው ግጭት ለማናገር ያደረግኘው ጥረት አልተሳካም።
በዚህ ግጭት ምክንያት ወደ ከአዲስ አበባ ደሴ እና ከሰሜን ኢትዮጵያ ከተሞች ወደ አዲስ አበባ የትራንስፖርት እንቅስቃሴ ከቆመ አራተኛ ቀኑን ይዟል።