የአጣዬው ጥቃት “በከባድ የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ የተደራጀና ብዛት ባለው የታጠቀ ኃይል የተፈጸመ ነው”- የአማራ ክልል
ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠር እየሠራ እንደሚገኝም ነው የገለጸው
ክልሉ ጥቃቱ በኦነግ እና መሰል ተባባሪ አባላቱ መፈጸሙንም የክልሉ መንግስት አስታውቋል
ከሰሞኑ በአጣዬ እና አጎራባች የሰሜን ሸዋ አካባቢዎች የተፈጸመው ጥቃት በ “ኦነግ ቡድንና እሱን መሰል በሆኑ ተባባሪ አካላት”መፈጸሙን የአማራ ክልል መንግስት አስታወቀ፡፡
የክልሉ መንግስት ጥቃቱን የተመለከተ መግለጫ አውጥቷል፡፡
በመግለጫው በግለሰቦች መካከል ተቀስቅሶ ነገር ግን በእርቅ መፍትሔ አግኝቶ የነበረን ግጭት ምክንያት በማድረግ ከአርብ መጋቢት 10 ቀን 2013 ዓ.ም ጀምሮ በአጣዬ ከተማና በአካባቢው ሰላማዊ ዜጎች ላይ “ነውረኛ የሆነ ጥቃት” ተፈጽሟል ብሏል፡፡
“አርሶ አደር ይይዘዋል ተብሎ በማይጠበቅ ከባድና የቡድን መሣሪያ ጭምር በመታገዝ በተደራጀና ብዛት ባለው የታጠቀ ኃይል” መፈጸሙንም ነው በክልሉ መንግስት ኮሙኒኬሽን በኩል የወጣው መግለጫ ያመለከተው፡፡
የአካባቢው ህዝብ ለዘመናት በአብሮነት መኖሩን ያስታወሰው መግለጫው “ጥቃቱ በፍጹም ተቀባይነት የሌለው አደገኛና ከባድ ወንጀል ነው” ብሏል፡፡
በጥቃቱ ህይወት መጥፋቱንና ንብረት መውደሙን በመጠቆምም የክልሉ መንግሥት ጥልቅ ሀዘን እንደተሰማው ገልጿል፡፡
ጥቃቱ የክልሉ የፀጥታ መዋቅር ህግ በማስከበር የህልውና ዘመቻ ላይ ትኩረት አድርጎ እየተንቀሳቀሰ በሚገኝበት በተለይም በአጎራባች የትግራይ ክልል አካባቢዎች ተቆርጦ የቀረው የህወሓት ኃይል የተሚተነኩሰውን ግጭት ለመከላከል እቅስቃሴ እያደረገ ባለበት በዚህ ወቅት የተፈጸመ ነው እንደ ኮሙኒኬሽን ቢሮው ገለጻ።
ይህ የክልሉን ህዝብ እረፍት ለመንሳትና ሀገር ለማተራመስ በማሰብ የሚደረግ መሆኑን የክልሉ መንግሥት በሚገባ ይገነዘባልም ብሏል፡፡
ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመሆን ተጨማሪ የፀጥታ አካላትን ወደ ሥፍራው በማሰማራት ጥቃቱን ለመቆጣጠርና ንጹሐን ዜጎችን ለመታደግ አስፈላጊውን ሁሉ እየሠራ እንደሚገኝም ነው ያስታወቀው፡፡
የጥቃቱን ዝርዝር በፍጥነት አጣርቶ ለህዝቡ ይፋ እንደሚያደርግና አጥፊዎችን ሁሉ በቁጥጥር ሥር በማዋል ለህግ እንደሚያቀርብም ገልጿል፡፡
ህዝቡ ከመንግሥት ጎን እንዲቆምና መረጃ በመስጠት እንዲተባበርም ነው ጥሪ ያቀረበው፡፡