መከላከያ ሰራዊት ወደ አጣዬ እና አካባቢው እየገባ እንደሚገኝ ተገለጸ
በሁሉም የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢዎች ነው ባይባልም ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱን አቶ ሲሳይ ዳምጤ ተናግረዋል
“ሸዋሮቢት አካባቢ ተመሳሳይ ድርጊት ለመፈጸም ትንኮሳዎች እየተደረጉ ነው”-አቶ ሲሳይ ዳምጤ፣የአማራ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ
በአጣዬ እና በአካባቢው የተቀሰቀሰው ግጭት አጎራባች ወደሆነው የሸዋሮቢት ከተማ እና አካባቢው የመዛመት ዐይነት ሁኔታ እየታየበት ነው ተባለ፡፡
በሸዋሮቢት ከትናንት ጀምሮ የተኩስ እሩምታዎች እየተሰሙ መሆኑን የከተማው ነዋሪዎች ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ስማቸው እንዲገለጽ ያልፈለጉት ነዋሪዎቹ ከሸዋሮቢት ወጣ ብለው ወደ አጣዬ በሚያስኬደው የደሴ መንገድ ላይ በሚገኙ አነስተኛ የገጠርና የከተማ አካባቢዎች ላይ አሁንም የተኩስ ልውውጦች በመካሄድ ላይ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡
ትራንስፖርትን ጨምሮ ምንም አይነት እንቅስቃሴዎች መደረጋቸው እንደቆመም ነው የገለጹት፡፡
ይህን በአጣዬ ከተፈጸመው ጥቃት ጋር በተያያዘ ጉዳት የደረሰባቸውን ቤተሰቦቻቸውን ለመጠየቅ በሚል ወደ ስፍራው ጉዞ ቢጀምሩም ከሸዋሮቢት ለማለፍ እንዳልቻሉ ለአል ዐይን አማርኛ የተናገሩ ሌሎችም አረጋግጠዋል፡፡
ዙጢ ተብሎ ከሚጠራው የከተማው (ሸዋሮቢት) ቀበሌ ወጣ ብለው በሚገኙት የሰሜን ሸዋ እና የጅሌ ጥሙጋ አጎራባች አካባቢዎች በተለይም በባልጪ፣ በጀውሃ፣ ኩሪብሪ፣ በነጌሶ እና ሌሎች አካባቢዎች ከበድ ያሉ ችግሮች መኖራቸውንም ነው የገለጹት፡፡
“በተለይ የነጌሶ እና የኩሪብሪ አካባቢ ነዋሪዎች መኖሪያቸውን ለቀው እየወጡ ነው” ብለዋል አንድ ሌላኛው የመረጃ ምንጫችን፡፡
ጥቃት ፈጻሚው አካል ከባድ መሳሪያዎችን በመታጠቅ ጭምር ውጊያ መግጠሙንም ነግረውናል፡፡
ህክምና ለማግኘት በሚል ከነ ትጥቃቸው በአምቡላንስ ተጭነው ወደ ሸዋሮቢት ከመጡ የጅሌ ጥሙጋ አካባቢ ሰዎች ጋር በተያያዘ የተፈጠረው ችግር በከተማው ለተቀሰቀሰው ግርግር መንስዔ መሆኑንም ገልጸዋል ሰዎቹ ምናልባትም በአጣዬው ጥቃት ሲሳተፉ የነበሩ ሊሆኑ እንደሚችሉ በመጠቆም፡፡
አል ዐይን ከከተማ አስተዳደሩ ፖሊስ ጽህፈት ቤት ኢንስፔክተር መርሃጽድቅ ታዬን በስልክ ለማግኘት ሞክሮ ነበር፡፡
ሆኖም ኢንስፔክተር መርሃጽድቅ “አሁን ያለሁበት ሁኔታ አደገኛ ነው፤ ምንም ነገር ለመስጠት አልችልም ለህይወቴም ያሰጋኛል” በማለታቸው ሃሳባቸውን ለማካተት ሳይችል ቀርቷል፡፡
የሰሜን ሸዋ ዞን የጸጥታ አካላትን ለማናገር ያደረገው ጥረትም ኃላፊዎች “ስብሰባ ላይ” በመሆናቸው ሳይሳካ ቀርቷል፡፡
በዛሬ የኢቲቪ የምሳ ሰዓት ዜና እወጃ ላይ የስልክ ቃለ መጠይቅ ያደረጉት የአማራ ክልል የአስተዳደርና ጸጥታ ጉዳዮች ቢሮ ኃላፊ አቶ ሲሳይ ዳምጤ ዛሬ በሸዋሮቢት፣ ሰንበቴ እና ማጀቴ አካባቢዎች ላይ የተኩስ ልውውጦች እንደነበሩ ገልጸዋል፡፡
በሁሉም የሰሜን ሸዋ እና የኦሮሞ ብሄረሰብ ዞን አካባቢዎች ሊባል ባይችልም ሁኔታው እየተባባሰ መምጣቱንም ነው አቶ ሲሳይ የተናገሩት፡፡
በሸዋሮቢት እና በሌሎች አካባቢዎች ተመሳሳይ ጥቃትን ለመፈጸም ትንኮሳዎች እንዳሉም ጠቁመዋል፡፡
አቶ ሲሳይ የክልሉ መንግስት ማገዝ አለበት በሚል ለፌዴራል መንግስት ባቀረበው ጥያቄ መሰረት የመከላከያ ሰራዊት ወደ አካባቢው እየገባ እንደሚገኝም ተናግረዋል፡፡
ህዝቡ ባልተገባና በተሳሳተ መንገድ ወደ ሁከትና ብጥብጡ እንዳይገባ ሊጠነቀቅ እንደሚገባም ኃላፊው አሳስበዋል፡፡