አትሌት ደራርቱ ቱሉ “የትግራይ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ” መንግስት መንገድ እንዲከፍት ጠየቀች
ደራርቱ ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ችግሩን ይቀርፋሉ ብላ እንደምታምንም ተናግራለች
አትሌት ደራርቱ በትግራይ ክልል ልምምድ መስራት ያለባቸውና ወደ አዲስ አበባ መምጣት ያለባቸው አትሌቶች እንዳሉም ተናግራለች
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ኮማንደር አትሌት ደራርቱ ቱሉ የትግራይ አትሌቶች ከቤተሰቦቻቸው ጋር እንዲገናኙ የኢትዮጵያ መንግስት መንገድ እንዲከፈት ጠየቀች፡፡
አትሌት ደራርቱ ይህን ያለችው በ18ኛው የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አባላት በብሄራዊ ቤተ መንግስት በተዘጋጀው የሽልማት መርሀ-ግብር ነው፡፡
“የትግራይ አትሌቶች ቤተሰብ የማግኘት እድል አሁንም አላገኙም” ያለችው አትሌት ደራርቱ መንግስት ይህንን ችግር ይቀርፋል ብላ እንደምታስብም ተናግራለች፡፡
“ክብርት ፕሬዝዳንታችን በእርግጠኝነት ይህንን ነገር ይቀርፋሉ ብየ እገምታለሁ”ም ነው ያለችው ደራርቱ፡፡
አትሌት ደራርቱ፤ ደስታችን እውን እንዲሆንና ለሚቀጥለው ውድድር በሙሉ ልብ እንድንሰለፍ በትግራይ የሚገኙ አትሌቶች ባሉበት ስራቸው እንዲጀምሩ እንዲሁም መምጣት ያለባቸው አትሌቶች ደግሞ እዚህ እንዲመጡ ማድረግ አስፈላጊ ነውም ብላለች፡፡
መንግስት ሁሉም መሰረታዊ ነገሮች እንዲከፍትም ጠይቃለች አትሌት ደራርቱ ቱሉ፡፡
የትግራይ ክልል መንግስት አትሌቶቹ ቤተሰቦቻቸው ለማግኘት የሚያስችላቸው ሁኔታ ያመቻቻል ብላ እንደምታስብም አትሌት ደራርቱ ተናግራለች፡፡
በ18ኛው የዓለም አትሌቲክሰ ሻምፒዮና በድል ለተመለሰው የአትሌቲክስ ልዑካን ቡድን አባላት በብሄራዊ ቤተ መንግስት ከ50 ሺ እስከ አስከ 2 ነጥብ 75 ሚሊዮን ብር ድረስ ሽልማት ተበረክቶላቸዋል፡፡
በዚሁ መሰረት የወርቅ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች 1 ነጥብ 75 ሚሊዮን ብር ፣የብር ሜዳሊያ ላስመዘገቡ አትሌቶች 1 ሚሊዮን ብር እንዲሁም የነሃስ ሜዳሊያ ላመጡ አትሌቶች 700 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡
ክብረ ወሰን ላሻሻሉ አትሌቶች ደግሞ ተጨማሪ የ250 ሺ ብር ሽልማት ተበርክቶላቸዋል፡፡ በ10ሺ ሜትር ሜዳሊያ ውስጥ ባትገባም አትሌት ለተሰንበት ግደይ ወርቅ እንድታገኝ ወሳኝ የቡድን ስራ የሰራችው አትሌት እጅጋየሁ ታዬ እና አትሌት ሰንበት ግደይ በ5ሺ ሜትር ለነበራት የቡድን ስራ እያንዳንዳቸው የ500 ሺህ ብር ሽልማት አግኝተዋል፡፡
የአትሌቲክስ ቡድኑ አባል ሆነው የተጓዙ፣ አሰልጣኞች፣ተሳታፊ አትሌቶች፣ድፕሎማ ያመጡ አትሌቶችም የተለያየ መጠን ያለው የገንዘብ ሽልማት ተበርቶላቸዋል፡፡
ሽልማቱን ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና የባህልና ስፖርት ሚኒስትር አቶ ቀጄላ መርዳሳ አበርክተዋል፡፡
በፌደራል መንግስትና በህወሓት በካከል በተቀሰቀሰው ጦርነት ምክንያት ከትግራይ ወደ መሀል ሀገር ያለው የየብስና የአየር የህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት እንደተዘጋ ነው።
ጦርነት የነበሩት ላይ የገበሩት የፌደራል መንግስት ግጭቱን በሰላሚዊ መንገድ ለመፍታት መወሰናቸውን በተናጠል መግለጻቸው ይታወሳል።