በኦሪጎን የተገኘው ውጤት ለመላው ኢትዮጵየውያን ያበረከትነው የአዲስ ዓመት ስጦታ ነው- አትሌት ደራርቱ ቱሉ
ደራርቱ ቱሉ ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና ታሪክ ከፍተኛ ውጤት ማስመዘገቧን ገለፀች
ኢትዮጵያ በኦሪጎን አትሌቲክስ ሻምፒዮና እስካሁን በ4 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ2 ነሃስ ከዓለም 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች
22ኛው የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና በአሜሪካዋ ኦሪጎን በመካሄድ ላይ ይገኛል።
በውድድሩ ላይ ኢትዮጵያ እስካሁን በ4 ወርቅ፣ በ4 ብርና በ2 ነሃስ በድምሩ በ10 ሜዳሊያዎች በመሰብሰብ ከአዘጋጇ አሜሪካ በመቀጠል ከዓለም 2ኛ ደረጃ ላይ ተቀምጣለች።
ሌሊት ላይ በተካሄደ የሴቶች 5000 ሜትር ውድድር አትሌት ጉዳፍ ጸጋዬ ለኢትዮጵያ አራተኛውን ወርቅ ያስገኘች ሲሆን፤ አትሌት ዳዊት ስዩም ደግሞ 3ኛ ደረጃን በመያዝ የነሃስ ሜዳሊያ ማስገኘቷ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት አትሌት ደራርቱ ቱሉ በፌዴሬሽኑ የማህበራዊ ትስስር ገጽ በሰጠችው መግለጫ፤ ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እንኳን ደስ አላችሁ ብላለች።
የሌሊቱን ውድድር በተመለከተ በሰጠችው አስተያየት ውድድሩ በተያዘ እቅድ መሰረት መካሄዱን እና አትሌት ለተሰንበት ግደይ ለድሉ መገኘት ትልቁን ሚና መጫወቷን አስታውቃለች።
ለተሰንበት ባለፈው 10 ሺህ ሜትር ላይ ከአትሌት እጅጋየሁ ታዬ ጋር በሰሩት ጠንካራ የቡድን ስራ የወርቅ ሜዳለያ ማስገኘታቸውንም አስታውሳለች።
በሻምፒዮናው ላይ አንዳአንድ አትሌቶች ሁለት ጊዜ እንዲወዳደሩ መደረጉን እና ይህም የአትሌቶች ውጤት እና አቋም ላይ በመመስረት ኢትዮጵያን በማሰቀደም የተሰራ ነው ብላለች።
“በዚሀም በወሰድነው አቋም ድል ማምጣት ችለናል፤ ይህንን ስናደርግ ያስቀየምናቸው ሰዎች ሊኖር ይችላል፤ ያስቀየምነውን ሁሉ በእግዝአብሄር ስም ይቅርታ እጠይቃለሁ” ስትል ተናግራለች።
ውድድሩ ሊጠናቀቅ አንድ ቀን መቅረቱን እና በቀሪው ቀንም ኢትዮጵያውያን የሚሳተፉበት የሴቶች 800 ሜትር እና በወንዶች 5000 ሜትር ውድድር የተሻለ ውጤት እንደሚመጣ እርግጠኛ መሆኗንም አስታውቃለች።
በኦሪጎን የዓለም አትሌቲክስ ሻምፒዮና የተገኘው ውጤት ኢትዮጵያ በዓለም አትሌቲክ ሻምፒዮና ታሪክ ያገኘችው ከፍተኛ ውጤት መሆኑን እና ይህም የሁሉም አትሌቶች፣ የልኡካን ቡድኑ አባላት እና የአትሌቶች ቤተሰቦቸ ውጤት ነው ብላለች።
2015 አዲስ ዓመት ለመግባት አንድ ወር መቅረቱን በመንሳትም በሻምፒዮናው የተገኘው ውጤት ለመላው ኢትዮጵያውን ለአዲስ ዓመት ያበረከትነው ስጦታ ነው ስትልም ተናግራለች።
መላው ኢትዮጵያውን በተለይም በአሜሪካ በኦሪገን እና አካባቢው ለሚኖሩ ኢትዮጵያውን እና ትውልደ ኢትዮጵያውያን ድጋፍ አቅም መሆኑን በመግለጽ፤ ሁሌም ከአትሌቲክሱ ጎን ስለሆኑ አመስግናለች።
ኢትዮጵያ ሁሌም በልጆቿ ትሳቅ፣ ትክበር፣ ትደሰት፣ ከፍ ትበል ያለችው ደራርቱ ቱሉ፤ በ2015 አዲስ ዓመት በሀገሪቱ የሚሰሙ ጦርነቶች፣ ሞት፣ መፈናቀል የማይሰማበት፤ የድስታ፣ የፍቅር እና የድል እንዲሆን ተመኝታለች።