የበጎ ሰው ሽልማት በተለያዩ ዘርፎች በጎ ስራ የሠሩ ሰዎች እውቅና የሚሠጥበት መርሃ ግብር ነው
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የ2014 ዓ.ም የበጎ ሰው ልዩ ተሸላሚ በመሆን ዛሬ ተሸልማለች።
10ኛው የዓመቱ በጎ ሰው ዕውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር በዛሬው እለት በኢንተርሌግዥሪ ሆቴል ተካሂዷል።
በመርሃ ግብሩ ላይም አትሌት ደራርቱ ቱሉ በስፖርቱ ዘርፍ አመራር ባስመዘገበችው የላቀ ውጤት የበጎ ሰዉ የዓመቱ ልዩ ተሸላሚ ለመሆን በቅታለች።
ፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ ለአትሌት ደራርቱ ቱሉ የክብር ሽልማቱን በመርሃ ግብሩ ላይ ተገኝተው አብርክተዋል።
አትሌት ኮማንደር ደራርቱ ቱሉ የባህር ዳር ዩኒቨርሲቲ ኢትዮጵያን ብሎም አፍሪካን በስፖርቱ ዓለም በማስጠራት ጀምራ ለኅብረተሰብ ፍቅርና አንድነት መጎልበት በመትጋቷ የዓመቱን የክብር ዶክትሬት እንደሰጣት ይታወሳል።
ከ50 ዓመት በፊት በአርሲ በቆጂ የተወለደችው ደራርቱ ቱሉ ለአፍሪካ ሴት አትሌቶች ፈር ቀዳጅ ስፖርተኛ ናት።
በዓለም አቀፍ የስፖርቱ ማህበረሰብ የ10 ሺህ ሜትር ውድድር ንግስት በመባል የምትጠራው ደራርቱ በ10 ሺህ ሜትር የመጀመሪያውን የወርቅ ሜዳሊያ በፈረንጆቹ 1990 ላይ ቡልጋሪያ በተካሄደ የወጣቶች ውድድር ነበር።
ከዚህ ጊዜ ጀምሮም በተካሄዱ ውድድሮች ለሀገሯ 15 በላይ የወርቅ ብር እና ነሀስ ሜዳሊያዎችን በተለያዩ ውድድሮች ላይ ለሀገሯ አስገኝታለች።
በተያያዘ ዜና 10ኛው የዓመቱ በጎ ሰው ዕውቅና እና ሽልማት መርሃ ግብር በዘጠን ዘርፎቸች የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት አሸናፊዎቹ ሽልማታቸውን ተቀብለዋል።
በዚህም
1. በትምህርት ዘርፍ ዶ/ር ውብሸት ዠቅያለ፣
2. በበጎ አድራጎት ዘርፍ ወ/ሮ ክብራ ከበደ፣
3. በቅርስና ባህል ዘርፍ ሼህ መሀመድ አወል ሀምዛ
4. በኪነ ጥበብ ዘርፍ ዓለምፀሀይ በቀለ
5. በዳያስፖራ ዘርፍ ዶ/ር ርብቃ ጌታቸው
6. በንግድና ሥራ ፈጠራ ዘርፍ አቶ ሰይድ መሃመድ
7. በመንግሥትዊ የስራ ኃላፊነት ዘርፍ አቶ ግርማ ዋቄ
8. ሚዲያ ጋዜጠኝነት አቶ ሰለሞን ገ/ስላሴ እና
9. በሳይንስ ዘርፍ ኤመሬተስ ፕሮፌሰር ረዳ ተ/ሃይማኖት የዓመቱ የበጎ ሰው ሽልማት ተሸላሚ ሆነዋል።