በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ተጠባቂ አትሌቶች እነማን ናቸው?
የዘንድሮው ዓለም አቀፍ አትሌቲክስ ውድድር ነገ በሀንጋሪ መዲና ቡዳፔስት ይጀመራል
ኢትዮጵያዊያን በውድድሩ የመጀመሪያው ቀን ከሚወዳደሩ አትሌቶች መካከል ተጠቃሽ ናቸው
በቡዳፔስቱ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ላይ ተጠባቂ አትሌቶች እነማን ናቸው?
በየሁለት ዓመት አንዴ የሚካሄደው የዓለም አትሌቲክስ ውድድር ነገ በምስራቅ አውሮፓዋ ሀንጋሪ ዋና ከተማ ቡዳፔስት ይጀመራል፡፡
በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያን ጨምሮ የዓለማችን ሀገራት አትሌቶቻቸውን የሚያሳትፉ ሲሆን የመክፈቻው ውድድር የወንዶች 20 ኪሎ ሜትር የእርምጃ ፍጻሜ ውድድር እንደሚካሄድ ተገልጿል፡፡
ኢትዮጵያን ጨምሮ በርካታ ሀገራት የሀገራቸውን ሰንደቅ አላማ ከፍ ለማድረግ ወደ ስፍራው የተጓዙ ሲሆን የኢትዮጵያ አትሌቲክስ ቡድን በ11 የውድድር አይነቶች እንደሚወዳደሩ ይጠበቃል፡፡
ነገ ምሽት 3፡55 ላይ የሴቶች 10 ሺህ የፍጻሜ ውድድር እንደሚካሄድ የዓለም አትሌቲክስ ውድድር መርሃብብር ያስረዳል፡፡
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በውድድሩ ላይ ጎልተው ሊታዩ ይችላሉ የተባሉ 10 አትሌቶች ከወዲሁ የብዙሃን መገናኛዎችን ትኩረት ስበዋል ተብሏል፡፡
ጎልተው ይወጣሉ ከተባሉ አትሌቶች መካከል ከአፍሪካ የኢትዮጵያ ቦትስዋና እና ኬንያ አትሌቶች ሲጠቀሱ አሜሪካዊያኗ የ100 ሜትር ሯጭ ታማሪ ዴቪስ፣ ሰርቢያዊቷ የዝላይ ተወዳዳሪ አንጀሊና ቶፒች እንዲሁም ብሪታንያው የ800 ሜትር ተወዳዳሪ ማክስ በርጊን ተጠቅሰዋል፡፡
ኢትዮጵያዊቷ የ1 ሺህ 500 ሜትር ተወዳዳሪዋ ብርቄ ሀይሎም፣ የኬንያዊው የ800 ሜትር ተወዳዳሪ ኢማኑኤል ዋንዮንዪ እንዲሁም የቦትስዋናው ሌስሊ በ100 እና 200 ሜትር ውድድሮች ላይ በቡዳፔስት ይደምቃሉ ተብለው የተጠበቁ አትሌቶች ናቸው፡፡
ከነሀሴ 13 እስከ 21 ቀን 2015 ዓ.ም በሚካሄደው በዚህ ውድድር ላይ ኢትዮጵያ በ11 የውድድር አይነቶች ላይ አትሌቶቿን እንደምታሳትፍ የተገለጸ ሲሆን ከኬንያዊያን፣ ኔዘርላንድ እና ሌሎች ሀገራትን ወክለው ወደ ውድድር ስፍራው ያመሩ አትሌቶች ብርቱ ተፎካካሪዎች እንደሚሆኑ ይጠበቃል፡፡
ኢትዮጵያ በተለይም በ10 ሺህ እና 5 ሺህ ሜትር በሁለቱም ጾታ፣ በማራቶን በሁለቱም ጾታዎች እንዲሁም በሌሎች የውድድር ፕሮግራሞች ላይ ለሜዳሊያ ትጠበቃለች፡፡