ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በጣሊያን ሮም ጎዳና ለአትሌት አበበ ቢቂላ ማስታወሻ አኖሩ
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ "ሻምበል አበበ ቢቂላ የሀገር ኩራት ምንጭ እና ፈርጥ ነው"ብለዋል
ጠ/ሚኒስትር ዐቢይ በጣልያን እየተካሄደ በሚገኘው ዓለም አቀፍ የልማት እና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ ነው
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በጣሊያን መዲና ሮም ጎዳና ለአትሌት አበበ ቢቂላ ማስታወሻ አኖሩ።
በሚገኘው ዓለም አቀፍ የልማት እና የፍልሰት ኮንፈረንስ ላይ እየተሳተፉ የሚገኙት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሮም በአበበ ቢቂላ በተሰየመ ጎዳና ላይ ነው ማስታወሻውን ያኖሩት።
ይህን ተከትሎ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ "ሻምበል አበበ ቢቂላ የሀገር ኩራት ምንጭ እና ፈርጥ ነው"ብለዋል።
በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ለዘመናት የኢትዮጵያን ስም ያስነሣ እና ለአፍሪካውያን አትሌቶች በር የከፈተ ዕንቁ ሯጭ ነው ሲሉም አስፍረዋል።
አትሌቱ የጽናትና የአይበገሬነት ተምሳሌት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ጣልያን ሮም ከተማ በስሙ የተሰየመ ጎዳና አለው ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዛሬ በስፍራው የእርሱን ማስታወሻ አኑረናል ብለዋል።
ሻምበል አበበ ቢቂላ 17ኛው የኦሎምፒክ ውድድር እኤአ በ1960 በጣልያን መዲና ሮማ ሲካሄድ በባዶ እግሩ ሮጦ በማሸነፍ ነበር ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን በአትሌቱ ዘርፍ በር ከፋች መሆን የቻለው።
ሻምበል አበበ በቂላ በ1964 በቶክዮ ጃፓን በተካሄደው ውድድርም የራሱን ክብረወሰን በማሻሻል አሸናፊ መሆንም ችሏል።
አለምን በባዶ እግር ሮጦ በማሸነፍ አንቱታ ያተረፈውን ሻምበል አበበ በቂላ በገጠመው የመኪና አደጋ ምክንያት በ41 ዓመቱ ከዚህ አለም በሞት መለየቱም ይታወሳል።