በሙርሌ ጎሳ አባላት ጥቃት በተፈጠረው ግጭት የሟቾች ቁጥር በከፍተኛ መጠን ሊያሻቅብ ይችላል ተብሏል
በደቡብ ሱዳን የእርስ በእርስ ግጭት በትንሹ 242 ሰዎች ተገደሉ
በደቡብ ሱዳን ጆንግሌይ ግዛት ኡሮር በተሰኘ አካባቢ በተለያዩ መንደሮች በቅርቡ በተፈጸሙ ጥቃቶች ቢያንስ 242 ዜጎች መገደላቸውን የመንግስት ባለሥልጣን አስታወቁ ፡፡
ሪፖርቶች እንደሚያመለክቱት ከታላቁ የፒቦር አስተዳደር አካባቢ (Great Pibor Administrative Area) በመነሳት የሙርሌ ወጣቶች ባለፈው ቅዳሜ ጠዋት በኡሮር አካባቢ በሚኖሩ የ ሉው ኑዌር በርካታ መንደሮች ላይ ጥቃት እንዳደረሱ ነው፡፡
የሙርሌዎችን ጥቃት ተከትሎ፣ በሙርሌ እና ሉው ኑዌር መካከል ተከታታይ ተከታታይ ግጭቶች በተለያዩ መንደሮች ውስጥ መካሄዳቸውን የሀገሪቱ መገናኛ ብዙሀን ራዲዮ ታማዙጅ ዘግቧል፡፡
የሟቾችን አስከሬን የማፈላለግ እና የማሰባሰብ ስራ በመከናወን ላይ እንደሚገኝ የገለጹት የአካባቢው ባለስልጣናት እስካሁን 242 ሰዎች መሞታቸው እንደተረጋገጠ ተናግረዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ 370 ሰዎች መቁሰላቸውንም ባለስልጣናቱ አረጋግጠዋል፡፡
በሰላማዊ ሰዎች ላይ ባነጣጠሩት ጥቃቶች የሞቱ ሰዎች ቁጥር ሪፖርት ከተደረገው እጅግ ሊበልጥ እንደሚችል የመንግሥት ባለሥልጣናቱ ያስታወቁ ሲሆን ብዙ ሰዎች ከባድ የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸውም ተናግረዋል፡፡
በግጭቱ ምክንያት በርካታ ሰዎች መፈናቀላቸውን በመግለጽ ግጭት በተፈጠረባቸው ጉዳት ለደረሰባቸው ቤተሰቦች መንግስታዊ ያልሆኑ ግብረ ሰናይ ድርጅቶች ድጋፍ እንዲያደርጉ ባለስልጣናት ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ዘገባዎች እንደሚያሳዩት ለሞት ከተዳረጉት መካከል ሴቶችንና ሕፃናትን ጨምሮ ከ 200 በላይ የሚሆኑት የ ሉው ኑዌር ጎሳ አባላት ናቸው፡፡
በአካባቢው ጠንካራ አስተዳደር መስፈን አለመቻሉ በጎሳዎች መካከል ለሚፈጠሩ ግጭቶች ዋነኛው ምክንያት እንደሆነ ይነገራል፡፡
የሙርሌ ጎሳ አባላት ከዓመታት በፊት በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ጥቃት በመፈጸም በርካታ ሕጻናትን እና ከብቶች መዝረፋቸውን ተከትሎ የኢፌዴሪ መከላከያ ሰራዊት ከተወሰዱት ሕጻናት ብዙዎችን ማስመለሱ ይታወቃል፡፡