ደቡብ ሱዳን በኢትዮጵያ የተማሩትን ጄነራል ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አደረገች
አዲሱ የጦር መሪ ጄነራል ጆነሰን ጁማ ሀገራቸውን ለረዥም ዓመታት አገልግለዋል
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት በድንገት የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሽረት አድርገዋል
የደቡብ ሱዳን ፕሬዝዳንት በድንገት ነው የጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ሽረት አድርገዋል
የደቡብ ሱዳኑ ፕሬዚዳንት ሳልቫኪር ማያርዲት በድንገት አዲስ ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም መሾማቸው እያነጋገረ ነው፡፡ የሀገሪቱን የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ጄነራል ጋብሬል ጆክ ሪያክን ከኃላፊነት ማንሳታቸውና በድንገት በምትካቸው በኢትዮጵያ ከፍተኛ ወታደራዊ ትምህርት የወሰዱትን ጄነራል ጆንሰን ጁማ ኦኮትን የሀገሪቱ ጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም አድርገው ሾመዋል፡፡
በኢትዮጵያ ወታደራዊ ሥልጠና የወሰዱት ጄነራል ጆነሰን ጁማ አኮት በደቡብ ሱዳን ውስጥ ከፍተኛ ወታደራዊ ልምድ ካላቸው የጦር መኮንኖች መካከል አንዱ መሆናቸውን የህይወት ታሪካቸው ያስረዳል፡፡ በአውሮፓውያኑ 1987 በከፍተኛ ወታደራዊ ማዕረግ የተመረቁት አዲሱ ኤታማዦር ሹም ለኢትዮጵያና ለኡጋንዳ የተለየ ፍቅር እንዳላቸው ይገለጻል፡፡ የአንደኛ እና ሁለተኛ ደረጃ ትምህርታቸውን በአውሮፓውያኑ 1966 እስከ 1976 በኡጋንዳ ምስራቅና መካከለኛው ኢኳቶሪያል ነው የተከታተሉት፡፡ ኡጋንዳን የሚወዱትም ትምህርት የቀሰሙባት ሀገር ስለሆነች መሆኑ ነው የተገለጸው፡፡
አዲሱ የጦር መሪ በቀድሞው የደቡብ ሱዳን የነጻነት ታጋይ ጆን ጋራንግ ጊዜ ብዙ ወታዳራዊ ግዳጆችን መፈጸማቸው ይገለጻል፡፡ ጄኔራሉ በእንግሊዙ ካምብሪጂ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ዲግሪያቸውን ያገኙ ሲሆን ከጁባ ዩኒቨርሲቲም በደህንነትና ስትራቴጂክ ጥናት ሁለተኛ ድግሪ አላቸው፡፡
ታማዙጅ የተሰኘ የሀገሪቱ ራዲዮ እንደዘገበው አሁን ላይ በጁባ ዩኒቨርሲቲ በደህንነት ዘርፍ ማሻሻያ የሦስተኛ ድግሪ ትምህርት እየተከታተሉ ነው፡፡
ጄነራል ጆንሰን ጁማ ኦኮት በአውሮፓውያኑ 1984 የሱዳን ህዝብ ነጻነት ንቅናቄና ጦርን ተቀላቅለዋል፡፡
በኢትዮጵያ ጋምቤላ ክልል ኢታንግ የሁለተኛ ሌፍተናንት ጄነራልነት ማዕረግን አግኝተዋል፡፡