ጥቃት የደረሰበት ሆምስ የተባለው አካባቢ ከዚህ ቀደም የአይ ኤስ ዋነኛ ይዞታ እንደነበር የሚታወስ ነው
ጥቃት የደረሰበት ሆምስ የተባለው አካባቢ ከዚህ ቀደም የአይ ኤስ ዋነኛ ይዞታ እንደነበር የሚታወስ ነው።
በሶሪያ በታጣቂዎች በተከፈተ ተኩስ በጥቂቱ 53 ንጹሃን መገደላቸው ተገልጿል።
በማዕከላዊ ሆምስ ግዛት ለተፈጸመው ጥቃት የአይ ኤስ ታጣቂዎች ተጠያቂ ተደርገዋል።
የሶሪያው ብሄራዊ የዜና ወኪል ሳና እንደዘገበው፥ ንጹሃኑ ለምግብነት የሚውሉ ፍራፍሪዎችን ሲለቅሙ ነው ጥቃቱ የተከፈተው።
በተከፈተው ተኩስ ጉዳት የደረሰባቸውን ሁሉም ሰዎች ወደ ፓልሜራ ሆስፒታል ቢወሰዱም የተረፉት ጥቂቶቹ ናቸው ብሏል ዘገባው።
አምስት ከፍተኛ የመቁሰል አደጋ የገጠማቸውም ወደ ሌላ ሆስፒታል እንዲዛወሩ ተደርጎ ህክምና እየተደረገላቸው ይገኛል።
አንድ ከጥቃቱ የተረፈ ግለሰብ የአይ ኤስ ታጣቂዎች ተኩስ እንደከፈቱባቸው መናገሩን ሬውተርስ ዘግቧል።
አይ ኤስ ግን እስካሁን ለጥቃቱ ሃላፊነቱን እንደሚወስድ አላስታወቀም።
ንጹሃኑ የተገደሉበት ግዛት ሆምስ ከዚህ ቀደም በአይ ኤስ ይዞታ ስራ ከነበሩ አካባቢዎች የሚጠቀስ ነው።
ከአመታት በፊት አብዛኛውን የሶሪያ ክፍል ይዞ የነበረው አይ ኤስ ከሶስት ወገን በሚደርስበት የማጥቃት እርምጃ ከበርካታ ይዞታዎቹ ለቋል።
በሩሲያ የሚደገፉ የበሽር አል አሳድ መንግስት ሃይሎች በአንድ ወገን፥ የሶሪያ ዴሞክራሲያዊ ሃይሎች ደግሞ በአሜሪካ እየተደገፉ በቡድኑ ላይ ኪሳራ አድርሰዋል።
በቱርክ መንግስት የትጥቅ ድጋፍ የሚደረግላቸው ታጣቂዎችም በአይ ኤስ ላይ ጥቃት ማድረሳቸውን ቀጥለዋል።
በዚህም ቡድኑ የአጥፍቶ መጥፋትንና ፈጣን ጥቃት አድርሶ ማምለጥን ተያይዞታል።
12 አመት በሆነው የሶሪያ የእርስ በርስ ጦርነት ከ500 ሺህ በላይ ሰዎች እንደተገደሉ መረጃዎች ያሳያሉ፤ ከ6 ሚሊየን በላይ ሶሪያውያንም ሀገራቸውን ለቀው ለመሰደድ ተገደዋል።