የቻይና ኩባንያ ለ50 አመታት የሚያገለግል “አቶሚክ ባትሪ” ሰርቷል
በድጋሚ ሃይል መሞላት (ቻርጅ መደረግ) የማትፈልገው አነስተኛ ባትሪ ለስማርት ስልኮችም ሆነ ለድሮኖች ሁነኛ የሃይል ምንጭ ትሆናለች ተብሏል
አሜሪካና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በ1960ዎቹ የሰሯቸው አቶሚክ ባትሪዎች ግዙፍና አደገኛ እንደነበሩ ይነገራል
የቻይና ኩባንያ ቤታቮልት “ቢቪ100” የተሰኘ አቶሚክ ባትሪን አስተዋውቋል።
የሳንቲም ያህል መጠን ያላት አነስተኛ አቶሚክ ባትሪ ለ50 አመታት ያለምንም ሃይል መሞላት (ቻርጅ መደረግ) አገልግሎት ትሰጣለች ተብሏል።
አሜሪካ እና የቀድሞዋ ሶቪየት ህብረት በ1960ዎቹ አቶሚክ ወይም ከኒዩክሌር የሚሰሩ ባትሪዎችን ማምረት መጀመራቸውን መረጃዎች ያወሳሉ።
ከፕሉቱኒየም የሚሰሩት እነዚህ ባትሪዎች መጠናቸው ግዙፍ፣ ውድ እና አደገኛ የነብሩ ሲሆን፥ ከአመታት ማሻሻያ በኋላ የቻይናው ቤታቮልት ሳንቲም የምታክል ባትሪ ሰርቷል።
“አቶሚክ” የሚለው ስያሜ አስፈሪ ቢመስልም “ቢቪ100” ጨረር የማይለቅና ዘመኑን የዋጀ ስለመሆኑ አምራቹ ይገልጻል።
ባትሪው በተለይ ለአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ መሳሪያዎች፣ ለአነስተኛ ድሮኖች እና ሮቦቶች ሁነኛ የሃይል ምንጭ እንደሚሆንም ነው ያስታወቀው።
ዋጋው ምን ያህል እንዳልሆነ ያልተጠቀሰው የቤታቮልት አቶሚክ ባትሪ ስማርት ስልኮችን ሃይል መሙላትን ያስቀራልም ተብሏል።
ኩባንያው በድረገጹ ባሰፈረው ጽሁፍ” “አቶሚክ ባትሪያችን ስማርት ስልኮችን ድጋሚ ሃይል ሳይሞሉ፤ ድሮኖችም ሃይል ለመሙላት ማረፍ ሳይጠበቅባቸው ለ50 አመታት አስተማማኝ ሃይል ያቀርብላቸዋል” ብሏል።
የቻይናው ኩባንያ እስከ 230 አመት ሊያገለግሉ የሚችሉ አቶሚክ ባትሪዎችን ለመስራት ምርምሩን መቀጠሉን መግለጹንም ኦዲቲ ሴንትራል አስነብቧል።