በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም ቀጥሏል ተባለ
ለችግሩ ዕልባት ለመስጠት የደቡብ ክልል ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግስታት ጋር እየሰራ እንደሆነ የክልሉ ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ገልጿል
ትናንት አንድ ሰው መገደሉን እና በሰሞኑ ጥቃት የሟቾች ቁጥር 14 መድረሱን የወረዳው ኮሙኒኬሽን ጽ/ቤት አስታውቋል
በደቡብ ክልል አማሮ ልዩ ወረዳ በንጹኃን ዜጎች ላይ የሚፈጸመው ጥቃት አሁንም መቀጠሉን አል ዐይን አማርኛ ከተለያዩ ምንጮች አረጋግጧል፡፡
ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ በወረዳው ነዋሪዎች ላይ በሚፈጸሙ ጥቃቶች የተፈጠረው አለመረጋጋት ለተወሰኑ ጊዜያት ጋብ ብሎ ቢቆይም ፣ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ ዳግም አገርሽቶ ንጹሃን ህይወታቸውን በማጣት ላይ ናቸው፡፡
ወረዳውን ከሚያዋስነው ከኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ጉጂ ዞን “የቡድን መሳሪያዎችን ጭምር የታጠቁ ኃይሎች” ሰሞኑን ተደጋጋሚ ጥቃቶችን በመፈጸም ላይ መሆናቸውን የወረዳው የህዝብ ግንኙነት ጽ/ቤት ኃላፊ አዳምፍሬ ታሪኩ ተናግረዋል፡፡
አቶ አዳምፍሬ ከአል ዐይን አማርኛ ጋር በስልክ ባደረጉት ቆይታ ፣ የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም በአማሮ ወረዳ በሚኖሩ የኮሬ ህዝቦች እና በምዕራብ ጉጂ ህዝቦች መካከል እርቀሰላም ለመፍጠር ፣ በምዕራብ ጉጂ ዞን ገላና ወረዳ በነበረ ጉባዔ ላይ ታጣቂዎች በከፈቱት ተኩስ 6 ሰዎች መገደላቸውን አስታውሰዋል፡፡ የአማሮ ወረዳ የብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊን ጨምሮ የ6 ሰዎች ህይወት ከተቀጠፈበት ከዚህ ጥቃት በኋላ እስከትናንት ሚያዝያ 1 ቀን 2013 ዓ.ም በተፈጸሙ ጥቃቶች የ14 ንጹኃን ህይወት ማለፉንም ነው አቶ አዳምፍሬ የገለጹት፡፡
በንጹኃን ላይ የሚደርሰው ጥቃት እንዲቆም ፣ የደቡብ እና የኦሮሚያ ክልልን ጨምሮ የፌዴራል መንግስት ኃላፊነታቸውን እንዲወጡ ወረዳው በተደጋጋሚ አቤቱታ ማቅረቡን የገለጹት አቶ አዳምፍሬ ፣ ነገር ግን ችግሩ እልባት ከማግኘት ይልቅ እየተባባሰ መምጣቱን ተናግረዋል፡፡
መንግስት ችግሩን ከመፍታት ይልቅ ፣ “ለፖለቲካ ፍጆታ እየተጠቀመው” እንደሆነ ነው የአማሮ ወረዳ የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳምፍሬ የሚገልጹት፡፡
የደቡብ ክልል ሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ አቶ አለማየሁ ባውዲ ችግሩን በተመለከተ ለአል ዐይን በሰጡት አስተያያት ፣ አካባቢው የኦነግ ሸኔን ጨምሮ የተለያዩ የታጠቁ ኃይሎች በብዛት የሚንቀሳቀሱበት እንደሆነ ገልጸዋል፡፡ እነዚህ ታጣቂዎች በህብረተሰቡ ላይ በተቀናጀ መንገድ ጥቃት እንደሚፈጽሙ ተናግረው ፣ ኦነግ ሸኔን ለማስወገድ የኦሮሚያ የጸጥታ ኃይሎች እርምጃ ቢወስዱም የተሟላ ውጤት ማምጣት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
አማሮ ወረዳ በሚዋሰንባቸው የምዕራብ ጉጂ ገላና እና ሱሮ በርጉዳ ወረዳዎች ባለው ግጭት እና በሰሞኑ ጥቃቶች የሞቱ ንጹኃን 14 መድረሳቸውን የአማሮ ወረዳ ቢያስታውቅም ፣ 12 ሰዎች መገደላቸውን ክልሉ ማረጋገጡን የተናገሩት አቶ አለማየሁ ፣ ችግሩን ለማስቆም የክልሉ መንግስት ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል መንግስታት ጋር በጋራ በመስራት ላይ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡
በአካባቢው የንብረት መዘራረፍን ጨምሮ ከግድያ ጋር የተያያዙ ወንጀሎች በ ”ኦነግ ሸኔ” ብቻ ሳይሆን ፣ ሸኔን ሽፋን በማድረግ በቡድን በተደራጁ ታጣቂዎች እና በግለሰቦችም ጭምር የሚፈጸሙ መሆናቸው ችግሩን ውስብስብ እንዳደረገውም ነው አቶ አለማየሁ የገለጹት፡፡
የደቡብ ክልል የሰላምና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊው አክለው እንዳሉት ፣ በአካባቢው ላለው ችግር በሁለት መንገድ ማለትም፡ በፖለቲካዊ መንግድ እና በጸጥታ መዋቅር አማካኝነት እልባት ለመስጠት ስራዎች እየተሰሩ ነው፡፡
ከጸጥታ መዋቅር አንጻር የፌዴራል ፖሊስ እና የደቡብ ልዩ ኃይል በስፍራው ተገኝቶ ጸጥታ የማስከበር ስራ በማከናወን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው ፣ ”ዋናው መፍትሔ ግን ፖለቲካዊ ነው” ብለዋል አቶ አለማየሁ፡፡ ከዚህ ቀደም ተፈጽመዋል ለተባሉ የተለያዩ ወንጀሎች የበቀል አጸፋዊ እርምጃ የሚመስሉ ድርጊቶች ፣ በግጭቱ ውስጥ በሚገኙ አካላት በሰፊው እየተከናወኑ እንደሚገኙም የገለጹ ሲሆን ፣ አርሶ አደሩ እና አርብቶ አደሩ ተቀናጅቶ ችግሮችን በፖለቲካዊ መንገድ በውይይት ሊፈታ እንደሚገባ እና ለዚህም ትኩረት መሰጠቱን አበክረው ገልጸዋል፡፡
በአጠቃላይ በአካባቢው ያሉትን የጸጥታ ችግሮች በተመለከተ በጥናት ላይ የተመሰረተ መፍትሔ ለማምጣት ክልሉ ከኦሮሚያ ክልል እና ከፌዴራል ፖሊስ ጋር ስራ መጀመሩንም ነው አቶ አለማየሁ ባውዲ የተናገሩት፡፡
የአማሮ ወረዳ ከምዕራብ ጉጂ ጋር ከሚዋሰንባቸው ቆላማ አካባቢዎች ከ2008 ዓ.ም መጨረሻ ጀምሮ ባሉ ግጭቶች እና ጥቃቶች ሳቢያ እስካሁን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው አመቺ ባልሆኑ መጠለያዎች የሚገኙ የኮሬ ተፈናቃዮች ቁጥር ወደ 50 ሺ ገደማ መድረሱን የወረዳው መረጃ ያመለክታል፡፡ በ4 ቀበሌዎች የሚገኙ ቤቶች እና የተለያዩ ንብረቶ ሙሉ በሙሉ መውደማቸውንም ለአል ዐይን የገለጹት የወረዳው የህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ አዳምፍሬ ፣ ከወረዳው ማዕከል ኬሌ በምዕራብ ጉጂ በኩል ወደ ዲላ እና ሀዋሳ የተዘረጋው የፌዴራል መንገድ ከተዘጋም ሰነባብቷል ብለዋል፡፡ ይህም አካባቢውን ለከፍተኛ ኢኮኖሚያዊ እና ማህበራዊ ቀውስ በመዳረግ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡ መንግስት “ቸልተኝነትን” መምረጡን በመግለጽ በችግር ላይ ለሚገኘው ለዚህ አካባቢ ልዩ ትኩረት እንዲሰጥ እና ተጎጂዎች የካሳ ድጋፍ ተደርጎላቸው ተፈናቃዮች ወደ ቀዬያቸው እንዲመለሱ ሊያደርግ ይገባልም ብለዋል፡፡ ከተፈናቃዮቹ መካከል 30 ሺህ የሚሆኑት ከቀዬያቸው ከተፈናቀሉ ከ4 ዓመታት በላይ ያስቆጠሩ ናቸው፡፡