የፌዴራል የጸጥታ ኃይል እስካሁን እንዳልደረሰላቸው ከጥቃት የተረፉ የባቦ ጋምቤል ነዋሪዎች ገለጹ
ነዋሪዎቹ የሟቾች ቁጥር መንግስት ካስቀመጠው 28 ሰው ይልቃል ብለዋል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ጠዋት ግድያውን አውግዘው፤ በፌደራልና በክልል ኃይል ጥምረት እርምጃ እየተወሰደ መሆኑን ገልጸዋል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን በባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ ነዋሪዎች አሁንም የጸጥታ ስጋት ውስጥ መሆናቸውን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ለደህንነታቸው ሲባል ስማቸውን ለመግለጽ ያልፈለጉት ነዋሪዎቹ ከሰሞኑ በደረሰው ጥቃት ከሞት መትረፋቸውን ገልጸው እስካሁን ግን የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት እንዳልደረሰላቸው አስታውቀዋል፡፡
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ለተፈጸመው ጥቃት መንግስታቸው የአጸፋ እርምጃ እየወሰደ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡ የአጸፋ እርምጃ በክልልና በፌዴራል መንግስታት ቅንጅት እየተከናወነ መሆኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ቢገልጹም፤ ያነጋገርናቸው ነዋሪዎች ግን እስካሁን ድረስ የፌዴራል ፖሊስም ሆነ የሀገር መከላከያ ሰራዊት በአካባቢያቸው አለመድረሱን ለአል ዐይን አማርኛ ገልጸዋል፡፡
ከትናንት በስቲያ በተፈጸመው ግድያ ከሞቱት ሰዎች ውስጥ እስካሁን ያልተቀበሩ እንዳሉ ያነሱት ነዋሪዎቹ፤ ዛሬ ሙሉ ቀን በጥቃቱ የሞቱትን ሰዎች አስክሬን ከየቦታው እያነሱ ሲቀብሩ መዋላቸውን ተናግረዋል፡፡
የሟቾችን ቁጥር በተመለከተ የኦሮሚያ ክልል 28 ናቸው ቢልም ነዋሪዎቹ ግን ቁጥሩ በክልሉ የተገለጸው ብቻ እንዳልሆነ ተናግረዋል፡፡ ክልሉ ቁጥሩን 28 ነው ማለቱ እንዳሳዘናቸው ያነሱት እነዚሁ ነዋሪዎች፤ “የተገደሉትን ሰዎች ቁጥር መቀነስ ለምን ያስፈልጋል“ ሲሉም ይጠይቃሉ፡፡
በጥቃቱ ቤተሰቦቻቸውን ያጡ ሰዎች የሟች ቤተሰቦቻቸውን ፎቶና ቪዲዮ በመቅረጻቸው ብቻ ታስረው እንደነበር የገለጹት ነዋሪዎቹ አሁንም ከፍተኛ የደህንነት ስጋት እንዳለባቸው ነው የተናገሩት፡፡
ነዋሪዎቹ፤ የፌዴራል መንግስት ጸጥታ እንዲያስከብርና በአካባቢው ሰላም እንዲሰፍን መስራት እንዳለበት ገልጸው ይህ ካልሆነ ግን በሰላም ሰርተው የሚኖሩበት ቦታ እንዲያመቻችላቸው ጠይቀዋል፡፡ ስማቸው እንዲጠቀስ ያልፈለጉት እነዚህ ነዋሪዎች “እኛ የፖለቲካ ሰዎች አይደለንም፤ ገበሬዎች ነን ፤ መንግስት ለምን አይደርስልንም? ” ሲሉ ትናንት ለአል ዐይን አማርኛ መናገራቸው ይታወሳል፡፡
የኦሮሚያ ክልል መንግስት በዞኑ ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ ቦኔ ቀበሌ፣ በንጹሃን ዜጎች ላይ ጥቃት መፈጸሙንና በዚህም 28 ሰዎች መሞታቸውን ገልጾ ነበር፡፡
የኦሮሚያ ክልል ፖሊስ ጥቃት አድራሾቹ ማክሰኞ ምሽት 50 ሰዎችን ከቤት በግድ በማውጣት 28 ሰዎች ገድለው፤12 ሰዎችን ማቁስላቸውን በትናንትናው እለት አስታውቋል፤ የአጸፋ እርምጃም መውሰዱን መግለጹ ይታወሳል፡፡