በሁሉም ቦታ ለደረሰው ጥቃት የአጸፋ እርምጃ እየተወሰደ ነው- ጠ/ሚ ዐቢይ
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በምእራብ ወለጋ ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት አውግዘዋል
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ በተፈጸመ ጥቃት የ28 ህይወት አልፏል
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አህመድ በኦሮሚያ ክልል በምእራብ ወለጋ ዞን በንጹሐን ዜጎች ላይ የደረሰውን ጥቃት እንደሚያወግዙ አስታወቅ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ ዛሬ ባወጡት መግለጫ “ሆን ብለው በሰዎች ላይ መከራና ስቃይ የሚጨምሩ ግለሰቦች እና ቡድኖች በምንፈልጋት ኢትዮጵያ ውስጥ ስፍራ የላቸውም” ብለዋል።
“መሥዋዕትነት እየከፈልንም ቢሆን የኢትዮጵያን አንድነት አጠናክረን ጉዟችንን እንቀጥላለን” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ፤ በሁሉም ቦታ በደረሰው ጥቃት አጸፋ እርምጃ በክልልና በፈዴራል መንግሥት ቅንጅት እየተወሰደ መሆኑንም አስታውቀዋል።
መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ በጥፋት ኃይሎች ወጥመድ ላለመውደቅ በማስተዋል እየተጓዘ፤ በእንደዚህ ዓይነት ጉዳዮች ከመንግሥት ጋር ተባብሮ ጥፋተኞችን ወደ ሕግ ለማቅረብ እና ግድያዎቹ ፈጽሞ እንዲቆሙ በትብብር እንዲሰራም ጥሪ አቅርበዋል።
በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ ወለጋ ዞን ባቦ ጋምቤል ወረዳ፣ በተፈጸመ ጥቃት የ28 ህይወት ማለፉን የክልሉ ፖሊስ ኮሚሽን በትናትናው እለት ማስታወቁ ይታወሳል።
ግድያው የተፈጸመው ማክሰኞ ምሽት 3 ሰአት አካባቢ ሲሆን 50 ሰዎችን በግድ ከቤታቸው በማስወጣት በፈጸሙት ጥቃት 28 ሰዎች ሲገደሉ፤ 12 ሰዎች ደግሞ መቁሰላቸውን ፖሊስ አረጋግጧል።
በጥቃቱ ሕይወታቸው ካለፈ ሰዎች መካከል 16 ወንዶችና 12 ሴቶች መሆናቸውም ነው የገለጹት።