በ24 ሰዓታት ምርመራ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው 88 ሰዎች 55ቱ የጉዞ ታሪክና ከታማሚ ጋር ግንኙነት የሌላቸው ናቸው
በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከቁጥጥር ዉጭ እየሆነ ነውን?
ባለፉት 24 ሰዓታት በተደረገ 4,048 የላቦራቶሪ ምርመራ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ተጨማሪ 88 ሰዎች ተገኝተዋል፡፡
አዲስ የተገኙትን ጨምሮ ባጠቃላይ የኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች ቁጥር 582 ደርሷል፡፡ ትናንት ቫይረሱ የተገኘባቸው ሁሉም ኢትዮጵያውያን መሆናቸውንም የገለጹት የጤና ሚኒስቴሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ ግለሰቦች የእድሜ ክልላቸው ከ 8 እስከ 75 ዓመት ሲሆን 51 ወንዶች እና 37 ሴቶች ናቸው ብለዋል፡፡
73 ሰዎች ከአዲስ አበባ፣ 8 ሰዎች ከትግራይ ክልል ፣ 4 ሰዎች ከኦሮሚያ ክልል ፣ 1 ሰው ከሀረር ክልል ፣ እንዲሁም 2 ሰዎች የድንበር ተሸጋሪ አሽከርካሪዎች መሆናቸውንም ሚኒስትሯ ገልጸዋል፡፡
ከ88ቱ ግለሰቦች 13ቱ የውጭ ጉዞ ታሪክ ያላቸው፣ 20ው በቫይረሱ ከተያዘ ሰው ጋር ግንኙነት የነበራቸው፣ 55ቱ ደግሞ የጉዞም ይሁን የግንኙነት ታሪክ የሌለው እንደሆነ ሚኒስትሯ በሪፖርታቸው አካተዋል፡፡ በሌላ በኩል 1 ሰው ከኦሮሚያ ክልል ከቫይረሱ ያገገመ ሲሆን አጠቃላይ ያገገሙት ቁጥርም 152 ደርሷል፡፡
የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክ እና ከበሽተኛ ጋር ንክኪ ከሌላቸው 55 ታማሚዎች መካከል 53ቱ ከአዲስ አበባ ናቸው፡፡
ባለፉት ጥቂት ቀናት ቫይረሱ ከተገኘባቸው ሰዎች መካከል አብዛኛው የውጭ ሀገር የጉዞ ታሪክም ሆነ ከበሽተኛ ጋር ንክኪ የሌላቸው መሆናቸው የወረርሽኙን ስርጭት አሳሳቢነት የሚያመለክት ነው፡፡ ከፍተኛ የታማሚዎች ቁጥር ሪፖርት የተደረገባቸውን ሁለት ቀናት (የዛሬ ግንቦት 16/2012 ዓ.ም እና የትናንት) መረጃ ብቻ ለአብነት ብንመለከት በሁለቱ ቀናት በቫይረሱ መያዛቸው ከተረጋገጠ 149 ሰዎች 100ው (ከ 67 %) በላይ የሚሆኑት የጉዞና የንክኪ ታሪክ የሌላቸው ናቸው፡፡ ይሄም ወረርሽኙ ማህበረሰባዊ መሰረት እየያዘ መሆኑን እና ለቁጥጥር ወደ ሚያዳግት ደረጃ እየተሸጋገረ መሆኑን የሚያሳይ ሀቅ ነው፡፡
እስካሁን በኢትዮጵያ የተደረገው የኮሮና ቫይረስ የላቦራቶሪ ምርመራ 81,010 ነው፡፡ በምርመራው ቫይረሱ ከተገኘባቸው 582 ሰዎች መካከል ደግሞ 5 ሰዎች ሞተዋል ፤ 2 ሰዎች (ጃፓናውያን) ወደ ሀገራቸው ተመልሰዋል ፤ 152 ሰዎች አገግመዋል፡፡ በመሆኑም አሁን ላይ በለይቶ ህክምና ዉስጥ የሚገኙ ሰዎች ቁጥር 423 ነው፡፡
አጠቃላይ እስካሁን በኢትዮጵያ ከተገኙ የቫይረሱ ታማሚዎች መካከል 377 ሰዎች (65 በመቶ ገደማ) ከአዲስ አበባ ናቸው፡፡
በአዲስ አበባ ከተማ በሁሉም ክፍለ ከተሞች ኮሮና ቫይረስ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸው ትናንት በጤና ሚኒስትሯ ዶ/ር ሊያ ታደሰ የተገለፀ ሲሆን ፤ ልደታ ክፍለ ከተማ በተጠቂዎች ቁጥር ቀዳሚዉን ደረጃ ይይዛል፡፡ መርካቶ የሚገኝበት አዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ደግሞ ሁለተኛ ደረጃ ላይ ነው፡፡
'ከጋምቤላ ክልል' ውጭ በሁሉም ክልሎች እና ሁለት የከተማ አስተዳደሮች ቫይረሱ የተገኘባቸው ሰዎች መኖራቸውንም ዶ/ር ሊያ ታደሰ ገልጸዋል፡፡