በቤት ለቤት ቅኝት ከ 3 ሚሊዮን በላይ ቤቶች መዳረሳቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ
በቤት ለቤት ቅኝት ከ 3 ሚሊዮን በላይ ቤቶች መዳረሳቸውን ጤና ሚኒስቴር ገለጸ
በአገር አቀፍ ደረጃ የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል በተካሄደው የቤት ለቤት ቅኝት ከሦስት ሚሊዮን በላይ ቤቶች መዳረሳቸውን የጤና ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡ ሚኒስትሯ ሊያ ታደሰ (ዶ/ር) በሃገሪቱ እየተካሄደ ባለው የቅኝት ሥራ ዳሰሳ እየተካሄደ ሲሆን የቫይረሱ ምልክት የታየባቸው 427 የሚሆኑ ሰዎች መለየታቸውን ተናግረዋል።
በጤና ኤክስቴንሽን፣ በግብርና ልማት ባለሙያዎች፣ በመምህራንና በሌሎች በጎ ፈቃደኞች ቅኝቱ እየተደረገ መሆኑንም የገለጹት ሚኒስትሯ ቅኝቱ የቫይረሱ ስርጭት በማኅበረሰቡ ውስጥ ያለበትን ሁኔታ ለማወቅ ያስችላል ብለዋል። ቫይረሱን ለመከላከል እየተካሄደ ባለው እንቅስቃሴ መጀመሪያ ትኩረት የተደረገው በአውሮፕላን ማረፊያዎች እና በየብስ ወደ አገር በሚገቡ ሰዎች ላይ እንደነበር ያስታወሱት ሚኒስትሯ፣ በሂደት ዳሰሳው በአዲስ አበባና በክልሎች እንዲስፋፋ መደረጉንም ገልጸዋል።
ምንም እንኳን በኢትዮጵያ በቫይረሱ የሚያዙ ሰዎች አብዛኛው ከውጭ የሚመጡና ከእነርሱ ጋር ግንኙነት ያላቸው ቢሆኑም፣ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው ሰዎች በቫይረሱ ተይዘው መገኘታቸውን ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል የሰዎችን ወደ ጤና ተቋማት ያለመሄድንና የተዳከመ አገልግሎት ለማሻሻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን ዶክተር ሊያ አመልክተዋል።
የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር ኤባ አባተ (ዶ/ር) በበኩላቸው የኮሮና ቫይረስ ምርመራ ጣቢያዎችን የማደራጀቱ ሥራ መጠናከሩ ገልጸዋል።
በዚህም በአሁኑ ወቅት የጣቢያዎቹ ቁጥር 20 መድረሳቸውንና የመመርመር አቅማቸው እያደገ መምጣቱን ተናግረዋል። ይህም በአገር አቀፍ ደረጃ የምርመራ አቅምን ያሳድገዋል ብለዋል። በኢትዮጵያ እስካሁን በቫይረሱ የተያዙ ሰዎች 117 ደርሰዋል። 25 ሰዎች ከበሽታው ያገገሙ ሲሆን፣ሦስት ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው አልፏል።
ምንጭ፡- ኢዜአ