በጋምቤላ ክልል ድጋሚ በተከሰተው ጊኒዎርም በሽታ ሰባት ሰዎች መያዛቸውን ክልሉ አስታውቋል
በጋምቤላ ክልል ድጋሚ በተከሰተው ጊኒዎርም በሽታ ሰባት ሰዎች መያዛቸውን ክልሉ አስታውቋል
በኢትዮጵያ በጋምቤላ ክልል የጊኒዎርም በሽታ ዳግም በወረርሽኝ መልክ መከሰቱን የክልሉ ጤና ቢሮ በዛሬው እለት አስታውቋል፡፡
የቢሮ ኃላፊ ካን ጋትሉዋክን ጠቅሶ የጋምቤላ ክልል ፕሬስ ሴክሬታሪያት ጽ/ቤት እንደገለጸው ባለፉት 27 ወራት በተደረገ ቅኝት “በሽታው በውሾችና በዝንጀሮ ላይ ሲከሰት እንደነበር“ ገልፀው በአሁኑ ሰዓት በጎግ ወረዳ ጎግ ዲፓች ቀበሌ ዱሌ ንዑስ መንደር በወረርሽኝ መልክ በሰባት ሰዎች ላይ መከሰቱን አመልክተዋል፡፡
በሽታው ዳግም ሊያገረሽ የቻለው በህብረተሰቡ መዘናጋት መሆኑን አቶ ካን ጋትሉዋክን ተናግረዋል፡፡
ጸ/ቤቱ የካርተር ሴንተር ጊኒዎርም ማጥፊያ ፕሮግራም ከጤና ሚኒስቴርና ከኢትዮጵያ ህብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ጋር በመሆን ጊኒዎርምን የማጥፋት ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ጸ/ቤቱ አስታውቋል፡፡
በኢትዮጵያ በ1986 ዓ.ም ስለበሽታው በተካሄደ የዳሰሳ ጥናት በወቅቱ 1129 ሰዎች በበሽታው መጠቃታቸውንና በ99 አካባቢዎች ተስፋፍቶ እንደነበር መረጃዎች ያሳያሉ፡፡
በወቅቱም የጋምቤላ ክልል ከተጠቀሱት አካባቢዎች 70 የሚሆኑትን፤ የደቡብ ክልል ደግሞ 29 በመያዝ በሽታውን በከፍተኛ ቁጥር በማስተናገድ ተጠቃሽ ነበሩ፡፡ እኤአ 1980ዎቹ ዓመተ ምህረት ውስጥ የጊኒዎርም በሽታ በ21 ሀገራት ውስጥ ተንሰራፍቶ ከ3 ነጥብ 5 ሚሊየን በላይ ሰዎች በበሽታው ተጠቅተው ነበር፡፡