የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ከ10 ዓመት በፊት ስሙን ወደ አፍሪካ ህበረት መቀየሩ ይታወሳል
በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 25፣1963 ነበር በ32 ፈራሚ ሀገራት የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የተመሰረተው፡፡
በኢትዮጵያዊው ክፍሌ ወዳጆ ጸሃፊነት ስራ የጀመረው ይህ ድርጅት በወቅቱ የኢትዮጵያ መሪ ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ወይም ጃንሆይ እና በጋናው የነጻነት ታጋይ ክዋሚ ንኩሩማህ አሸማጋይነት በአዲስ አበባ ከ60 ዓመት በፊት ተቋሙ እንዲመሰረት ትልቁን የመሪነት ድርሻ እንደሚወስዱ ታሪክ ያስረዳል፡፡
አውሮፓዊያን አፍሪካን ለመቀራመት ወደ አህጉሩ በመጡ 60ኛ ዓመታቸው ላይ የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት የጸረ ቅኝ ግዛት ትግሎችን ለመደገፍ፣ አፍሪካዊያንን ለማስተሳሰር እና ችግሮቻቸውን መፍታት ደግሞ የዚሁ ተቋም ዋና ዋና አላማዎችም ነበሩት፡፡
ከ10 ዓመት በፊት ስሙን ወደ አፍሪካ ህብረትነት የቀየረው ይህ ተቋም በ60 ዓመታት ውስጥ ምን አሳካ? ምንስ ሳያሳካ ቀረ? ዋነኛ ችግሮቹስ ምን ምን ናቸው? ቀጣይ ፈተናዎቹስ? ሲል ዓል ዐይን አማርኛ አፍሪካዊ ምሁራንን አነጋግሮ ተከታዩን ዘገባ አዘጋጅቷል፡፡
ደቡብ አፍሪካዊቷ ታንዶ ሶንግዌቩ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና አማካሪ ሲሆኑ ትኩረቱን በአፍሪካ የባህል እና ኦኮኖሚ ነጻነት ላይ ያደረገው ቻት አፍሪካ የተሰኘ አፍሪካዊ ተቋም መስራችም ናቸው፡፡
እሳቸው እንደሚሉት ቅድመ አያቶቻችን የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን የመሰረቱት በወቅቱ የነበረውን የቅኝ ግዛትን ለማስወገድ ብቻ አልነበረም ብለዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ አፍሪካ የኢኮኖሚ ባህል እና የፖለቲካ ነጻነት እንዲኖራቸው በሚል ነበር የሚሉት አማካሪዋ አፍሪካ አሁንም በተመሳሳይ ችግር ውስጥ መቀጠሏን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ባህል፣ ኢኮኖሚ እና ሌሎች ሀብቶች በምዕራባዊያን ቁጥጥር እና ጸጽዕኖ ስር ናቸው የሚሉት ታንዶ አፍሪካ አሁን ያለችበት ሁኔታ አያቶቻችን ከነበሩበትም ጊዜ የከፋ መሆኑን ጠቅሰዋል፡፡
በየትኛውም የአፍሪካ ሀገራት ብትጓዝ ለአብነትም ግዙፍ ገቢ የሚያስገኙ ተቋማት በምዕራባዊያን እንደተያዙ መሆናቸውን ትመለከታለህ፣ የምንለብሰው ልብስ፣ የምንጠቀመው ቴክኖሎጂ እና ምግቦቻችን ሳይቀር ከምዕራባዊያን ሀገራት የመጡ ናቸውም ብለዋል፡፡
የአፍሪካ አንድነት መስራቾች ዋና አላማቸው ከጥገኝነት የተላቀቀች የኢኮኖሚ ነጻነቷ የተረጋገጠች አፍሪካን እውን ማድረግ ነበር የሚሉት ደግሞ ግብጻዊቷ የአፍሪካ ቢዝነስ ካውንስል ፕሬዝዳንቷ ዶክተር አማኒ ኡስፉር ናቸው፡፡
አፍሪካ በሌሎች አህጉራት የማይገኙ ውድ የፋብሪካ ጥሬ እቃዎችን አሁንም በርካሽ እየላከች በውድ ዋጋ እያስገባች ነው የሚሉት ዶክተር አማኒ ይህ እየቀጠለ የኢኮኖሚ ነጻነት ሊረጋገጥ አይችልም ብለዋል፡፡
ዶክተር አማኒ አክለውም አፍሪካ የአውሮፓ ምርት ማራገፊያ ቀጥሏል የአፍሪካዊያን እርስ በርስ ንግድ ዝቅተኛ ነው፡፡ የአፍሪካ ሀገራት እርስ በርስ የንግድ ግንኙነት ከመመስረት ይልቅ ወደ አውሮፓ መላክ ይቀናቸዋልም ብለዋል፡፡
አፍሪካ በቀል የሆኑ የንግድ፣አቪየሽን፣ ቴክኖሎጂ እና ሌሎች አስፈላጊ ተወዳዳሪ ተቋማት ጥቂት መሆናቸውን የሚናገሩት ዶክተር አማኒ እሴት የተጨመረባቸው ምርቶችን መላክ እና የንግድ እና ቢዝነስ ስራዎችን ማቀላጠፍ የሚያስችሉ መሰረተ ልማቶች ላይ ካልሰራን የአፍሪካ ዘመናዊ ቅኝ ግዛት መቀጠሉ አይቀሬ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በአዲስ አበባ ዩንቨርሲቲ የአፍሪካ ጥናትና ምርምር መምህር የሆኑት ዶክተር ደቻሳ አበበ ከ60 ዓመት በፊት የተመሰረተው የአፍሪካ አንድነት ድርጅት በእስካሁኑ ጊዜ ቆይታው ስኬታማ ነበር ወይም ስኬታማ አይደለም ማለት እንደማይቻል ተናግረዋል፡፡
ድርጅቱ በእስካሁኑ ቆይታው ካሳቸው ነገሮች መካከል የተወሰኑ ሀገራት ከቅኝ ግዛት ነጻ እንዲወጡ እገዛ ማድረጉ፣ አፍሪካዊያን የሚሰባሰቡበት እና የሚመክሩበት ተቋም መሆኑ፣ በተወሰኑ ሀገራት መካከል ግጭቶች ሲከሰቱ በውይይት ለመፍታት መሞከሩ እና የሰላም ችግር ባለባቸው ሀገራት ሌሎች ተቋማትን እና ሀገራትን በማስተባበር ሰላም አስከባሪ ሀይል እንዲገባ ማድረጉን ዶክተር ደቻሳ ጠቅሰዋል፡፡
ይሁንና ድርጅቱ ከመጀመሪያውም ሆነ ከ10 ዓመት በፊት ስሙን ወደ አፍሪካ ህብረት ሲቀይር ተመሳሳይ እና ሊሻገረው ያልቻለው ችግሮች አሉበት የሚሉት ዶክተር ደቻሳ የቅኝ ገዢዎችን ፍላጎት ሊያሳካ በሚችሉ አንቀጾች መተብተቡን ጠቅሰዋል፡፡
“የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት ጀምሮ የስራ ቋንቋዎቹ የቅኝ ገዢዎችን ቋንቋ እንዲሆኑ መወሰኑ የመጀመሪያው ስህተት ነው“ ያሉት ዶክተር ደቻሳ ይህም ከምዕራባዊያን ተጽዕኖ እንዳይለቀቅ ዋነኛው ምክንያት መሆኑን አንስተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ እንግሊዘኛ፣ ፈረንሳይኛ፣ አረብኛ፣ ፖርቹጊዝ እና ስፓኒሽ የአፍሪካ ህብረት የስራ ቋንቋ ማድረግ ከአንድ ቢሊዮን ህዝብ በላይ ያለው አህጉርን የራሱ ባልሆነ ባህል እንዲዋጥ መፍቀድ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
አፍሪካ ወጣቶቿን በራሷ ቋንቋዎች ማስተማር እና ማሰልጠን የሚስችል የትምህርት ስርዓት ባለመቅረጿ ለምዕራባዊያን ተጽዕኖ እጅ የሰጠ እና የአውሮፓዊያንን ህይወት የሚናፍቅ ትውልድ ቀጥሏል፣ በዚህ ምክንያት የአያቶቻችን እቅድ እና ህልም መና መቅረቱን ዶክተር ደቻሳ ገልጸዋል፡፡
አሁን ያለው የአፍሪካ ህብረትም የቤተ ዘመድ ስብስብ ይመስላል የሚሉት ዶክተር ደቻሳ ህብረቱ ማሻሻያ ካላደረገ ሌላ 60 ዓመት እና ከዛ በላይ ጊዜን ሊያባክን እንደሚችል ተናግረዋል፡፡
ህብረቱ በተለይም በሀገራት የውስጥ ጉዳዮች ላይ ጣልቃ አለመግባት፣ ሀገራት በቅኝ ግዛት ዘመን የነበራቸውን ድንበር ይዘው እንዲቀጥሉ፣ የገንዘብ ድጋፎችን እና የስራ ቋንቋዎችን በሚመለከት ማሻሻያ ካላደረገ ለአፍሪካ የማይጠቅም እና የይስሙላ ተቋም ይሆናልም ብለዋል፡፡
በመሆኑም የአፍሪካ ህብረት የቅኝ ግዛት በደሎችን የሚስቀጥሉ ስምምነቶችን በማቆም የእርስ በርስ ንግድ እና ባህል ትስስሮችን የሚጎለብቱ፣ አፍሪካዊ የፈጠራ ቴክኖሎጂዎች እንዲወለዱ የሚያበረታቱ እና በሀገራት ችግሮች ዙሪያ እውነተኛ መፍትሄዎችን ማምጣት የሚያስችሉ አሰራሮችን መከተል እንደሚገባም ዶክተር ደቻሳ አክለዋል፡፡
አፍሪካ የራሷን ችግሮች በራሷ ልጆች መተንተን የሚስችል እውቀት መፍጠር እና ከምዕራባዊያን ስሪተ ትምህርት እና ቴክኖሎጂ ማላቀቅ የሚስችሉ አሰራሮችን በመዘርጋት የኢኮኖሚ፣ ትራንስፖርት እና ባህል ነጻነቶችን ለማረጋገጥ መስራት አለባትም ብለዋል፡፡
በፈረንጆቹ ዘመን አቆጣጠር ግንቦት 1963 በአዲስ አበባ የአፍሪካ አንድነት ድርጅት ሲመሰረት የ32 ሀገራት መሪዎች በተገኙበት ወቅት ጋምቢያዊው የፓን አፍሪካ ጽንሰ ሀሳብ አቀንቃኙ ጋምቢያዊው አሊዮ ኢብራሂም ቻም ጁፍ ተጋብዞ ንግግር አድርጎ ነበር፡፡
ይህ ፓን አፍሪካኒስት በወቅቱ ለነበሩት የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች “አውሮፓዊያን ከ75 ዓመት በፊት ነበር በጀርመን ተሰባስበው አፍሪካን ለመቀራመት የተሰባሰቡት፡፡
የአፍሪካ አንድነት ድርጅትን ለመመስረት የዘገየን ቢመስልም ጸረ ቅኝ አገዛዝን ከአፍሪካ እና ከዓለም አስወግደን ነገ የልጅ ልጆቻችን የሚኮሩበት ተቋም ይሆናል፡፡ አፍሪካን ከሌላ አዲስ ቅኝ ግዛት ታደጓት፣ ክብሯን እና መረጋጋቷን ጠብቁላት“ ሲል በመድረኩ ላይ ተናግሮ ነበር፡፡