ፕሬዝዳንት ፑቲን “አፍሪካ የአዲሱ የዓለም ስርዓት አንዷ መሪ ትሆናለች” ብለዋል
ሩሲያ ለአፍሪካ የ20 ቢሊዮን ዶላር እዳ ስረዛ ማድረጓን ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን አስታወቁ።
የሩሲያ ፕሬዚዳንት ቭላድሚር ፑቲን በቀጣይ በሞስኮ ሊካሄድ ስለታቀደው ሩሲያ እና አፍሪካ ጉባኤ ንግግር አድርገዋል።
ፕሬዝዳንት ፑቲን በዚህ ንግግራቸው ላይ እንዳሉት ሩሲያ ለአፍሪካ ሀገራት ያበደረችውን የ20 ቢሊዮን ብድር መሰረዟን ጠቅሰዋል።
አፍሪካ የአዲሱ የዓለም ስርዓት አንዷ መሪ ትሆናለች ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን ሩሲያ ለአፍሪካ ትኩረት ትሰጣለችም ብለዋል።
ሩሲያ፣ አፍሪካ፣ እስያ እና ደቡብ አሜሪካ የዓለማችን አብላጫ የህዝብ ብዛት ያላቸው ሀገራት ናቸው ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን፤ የምዕራባዊያንን አዲስ የቅኝ ግዛት አስተሳሰብም ይቃወማሉም ሲሉ ተናግረዋል።
ፕሬዝዳንቱ አክለውም ሩሲያ የአፍሪካን ምግብ፣ ማዳበሪያ እና ነዳጅ ፍላጎት ለመሸፈን ግዴታዋን እንደተወጣችም ጠቁመዋል።
ምዕራባዊያን ሀገራት ሩሲያ ለአፍሪካ ሀገራት የአፈር ማዳበሪያ በነጻ ለመስጠት እያደረገች ያለውን ጥረት ለማክሸፍ የተለያዩ መንገዶች ለማስተጓጎል መጣራቸውንም ፕሬዝዳንት ፑቲን ተችተዋል።
የስንዴ እና ማዳበሪያ ምርቶች ለተቸገሩ ሀገራት እንዲደርስ ሩሲያ እየጣረች ነው ያሉት ፕሬዝዳንት ፑቲን በጥቁር ባህር ከተጓጓዘው የስንዴ ምርት መካከል 45 በመቶው ወደ አውሮፓ ሀገራት መጓጓዙንም በንግግራቸው አክለዋል።