የሩሲያን ተጽዕኖ መግታት ያለመው የማክሮን የአራት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት
ከቀድሞው ቅኝ ግዛቶቿ ወታደሮቿን ለማስወጣት የተገደደችው ፈረንሳይ ፊቷን ወደ አንጎላ፣ ጋቦን እና ሁለቱ ኮንጎዎች አዙራለች
ማክሮን በሀምሌ ወር በሶስት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝት ማድረጋቸው ይታወሳል
የፈረንሳዩ ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን የአራት የአፍሪካ ሀገራት ጉብኝታቸውን ዛሬ ይጀምራሉ።
ማክሮን ከጋቦን ተነስተው አንጎላን እና ሁለቱን ኮንጎዎች ያዳርሳሉ።
በቀድሞ ቅኝ ግዛቶቿ የፈረንሳይ ጠል አመለካከቶች እያደጉ ሄደው ከቡርኪናፋሶ እና ማሊ ወታደሮቿን ለማስወጣት የተገደደችው ፓሪስ ሌሎች የአፍሪካ ሀገራትን ማማተር ይዛለች።
በሀምሌ ወር 2022 በካሜሮን፣ ቤኒን እና ጊኒ ቢሳው ጉብኝት ያደረጉት ፕሬዝዳንት ኢማኑኤል ማክሮን በዛሬው እለትም በአራት የመካከለኛው አፍሪካ ሀገራት የሚያደርጉትን ጉብኝት ይጀምራሉ ተብሏል።
- ከማሊና ቡርኪና ፋሶ የተባረረችው ፈረንሳይ ሌላ አፍሪካዊ ሀገር ፍለጋ ላይ መሆኗን ገለጸች
- የፈረንሳይን ጦር ያባረረችው ቡርኪናፋሶ የሩሲያውን ዋግነር ቡድን ተቀበለች
ፈረንሳይ በአፍሪካ የምትከተለውን ፖሊሲ ከትናንት በስቲያ ይፋ ያደረጉት ማክሮን፥ ከ50 በላይ ሀገራትን ባቀፈችው አፍሪካ “የጋራ ጥቅምን የሚያስከብር እና ሃላፊነት የሚሰማው ግንኙነት” ለመመስረት እንሰራለን ብለዋል።
ፓሪስ የቀደሙ የቅኝ ግዛት ፖሊሲዎቿን ለመሰረዝም ቃል ገብተዋል።
ማክሮን ለሁለተኛ የስልጣን ዘመን ለሚያደርጉት ፉክክር በአፍሪካ ላይ ትኩረት ስለማድረጋቸውም ማንሳታቸውን ፍራንሥ24 አስነብቧል።
በፈረንሳይ ቅኝ ተገዝተው በነበሩ ሀገራት እየገነነ የመጣውን “ጥላቻ” ማርገብ ላይም ማክሮን እየሰሩ ስለመሆኑ ተነግሯል።
ዛሬ በጋቦን የሚጀመሩት ጉብኝት ግን ሩሲያ በፈረንሳይኛ ተናጋሪ ሀገራት ተጽዕኖዋ እየጎላ መምጣቱ ከመነገሩ ጋር የተያያዘ ሊሆን እንደሚችል ተገምቷል።
ማክሮን በጋቦን በሚካሄደው የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ እንደሚሳተፉና ከፕሬዝዳንት አሊ ቦንጎ ኦንዲማ ጋር እንደሚወያዩ ይጠበቃል።
የጋቦን ጉብኝታቸውን እንዳጠናቀቁም ወደ ቀድሞ የፈረንሳይ ቅኝ ግዛት አንጎላ ያመራሉ ተብሏል።
ማክሮን በዲሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ እና ኮንጎ ብራዛቪል በሚኖራቸው ቆይታም በሳህል ቀጠና ተጽዕኖዋ እየደበዘዘ የመጣውን ፈረንሳይ ወደቀደመ ቦታዋ መመለስ የሚያስችሉ ምክክሮች ያደርጋሉ ብሏል አጃንስ ፍራንስ ፕሬስ።
ከማሊ እና ቡርኪናፋሶ ወታደሮቿን ለማስወጣት የተገደደችው ፈረንሳይ፥ በሩሲያ ይደገፋሉ ከምትላቸው የሀገራቱ ወታደራዊ መሪዎች ጋርም መካሰሷ ቀጥሏል።
በማሊ እና ማዕከላዊ አፍሪካ የሩሲያ ቅጥረኛ ወታደሮች (ዋግነር) እየተበራከቱ መምጣትንም በተደጋጋሚ ገልጻለች።
በአፍሪካ ሀገራት ከ6 ሺህ በላይ ወታደሮች ያሏት ፈረንሳይ በተለያዩ ሀገራት የሚገኙ ወታደራዊ ጣቢያዎቼን እዘጋለሁ ብትልም የሩሲያ ተጽዕኖ እያየለ መሄድ ግን ውሳኔዋን እንድትቀለብስ ሊያደርጋት እንደሚችል ተገምቷል።