ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ ውድቅ አደረገች
ህብረቱ በግድቡ ዙሪያ ለግብጽ ወግኖ ያወጣውን መግለጫ ድጋሚ እንዲያጤነው ኢትዮጵያ ጠይቃለች
የአውሮፓ ህብረት “የግብጽ ታሪካዊ የውሃ ድርሻ ሊነካ አይገባም” ብሏል
ኢትዮጵያ የአውሮፓ ህብረት በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ያወጣውን መግለጫ ተቀባይነት የሌለው መሆኑን አስታወቀች።
የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ቃል አቀባይ አምባሳደር ዲና ሙፍቲ መግለጫ ሰጥተዋል።
ቃል አቀባዩ በዚህ ጊዜ እንዳሉት ከሰሞኑ የአውሮፓ ህብረት እና ግብጽ በጋራ በህዳሴው ግድብ ዙሪያ ባወጡት መግለጫ ዙሪያ አስተያየት ሰጥተዋል።
አውሮፓ ህብረት በእስካሁኑ የህዳሴው ግድብ የሶስትዮሽ ውይይቱ ላይ ታዛቢ ነበር ያሉት አምባሳደር ዲና የሰሞኑ አስተያየት ግን ውግንናውን ለግብጽ በሚመስል መንገድ መግለጫ ሰጥቷል ብለዋል።
የአውሮፓ ህብረት ከግብጽ ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር እና ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጋር በመሆን የግብጽ ታሪካዊ የውሃ ድርሻ ሊነካ አይገባም ብሏል
ይህ አስተያየት ከአንድ የድርድሩ ታዛቢ አካል መሰጠቱ ውግንናው ላይ ጥያቄ እንድናነሳ አስገድዶናል ያሉት አምባሳደር ዲና ህብረቱ ከግብጽ ጎን ወግኖ የሰጠውን አስተያየት መልሶ እንዲያጤነው እንጠይቃለንም ብለዋል።
በኢትዮጵያውያን እና መንግስት ወጪ እየተገነባ ያለው ታላቁ የህዳሴው ግድብ ግንባታ 84 በመቶ መጠናቀቁ ይታወሳል።
ግንባታው በዚህ ደረጃ ላይ እያለም ከግድቡ ሁለት ተርባይኖች 700 ሜጋ ዋት ሀይል እንዲያመነጩ ለማድረግ በተደረገው ጥረት ከሶስት ወራት በፊት አንዱን ተርባይን ወደ ስራ በማስገባት 350 ሜጋ ዋት ሀይል ማመንጨት መጀመሩም አይዘነጋም።
ሶስተኛው የህዳሴው ግድብ ውሀ ሙሌት በሚቀጥለው ወር እንደሚጀመር መንግስት ከዚህ በፊት በሰጣቸው መግለጫ መናገሩ ይታወቃል።