ሱዳን በኢትዮጵያ የተገደሉባትን ወታደሮች አስመልክታ “ለፀጥታው ምክር ቤት ላመለክት ነው” አለች
ሱዳን ሉዓላዊነቴ እና የዜጎቼ ክብር ስለተነካ እርምጃ እወስዳለሁ ስትል አስጠንቅቃለች
በካርቱም የኢትዮጵያ አምባሳደር ስለጉዳዩ እንዲያብራሩም ሱዳን ጠርታለች
ሱዳን በኢትዮጵያ የተገደሉባትን ወታደሮች አስመልክታ ለጸጥታው ምክር ቤት እንደምታመለክት ገለጸች።
የሱዳን መከላከያ ቃል አቀባይ በትናንቱ መግለጫ እንዳለው “ሰባት የሀገሪቱ ጦር አባላት በኢትዮጰያ እንደተገደሉ እና የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ” መናገራቸው ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎም የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን አስመልክቶ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደሚያመለክት አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ለሌሎች ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት እንደሚያመለክትም ገልጿል።
እንዲሁም በካርቱም ያለውን የኢትዮጰያን አምባሳደር ለምን የሱዳን ጦር በኢትዮያ እንደተገደሉ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚቀበልም ሚኒስቴሩ አስታውቋል።
ሱዳን የዓለም አቀፍ ህግን በጣሰ መንገድ ምርኮኞችን በማሰቃይት እና በመግደል የከሰሰች ሲሆን የኢትዮጰያ ጦር የሱዳን ጦር ምርኮኞችን በመግደል፣ ንጹሃንን በማገት እና የሱዳንን ሉዓላዊ ግዛት ጥሳለች በሚል ክስ አቅርባለች።
“የሱዳን ሉዓላዊነት እና የዜጎቿ ሰብዓዊ ክብር ተደፍሯል” ያለው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ በዓለም አቀፍ ህግ መሰረት ሉዓላዊነቷን ለማስከበር እርምጃ እንደምትወስድም ጠቁማለች።
ይህ በዚህ እንዳለ ግን በሱዳን ክስ እና ወቀሳ የቀረበባት ኢትዮጵያ እስካሁን በጉዳዩ ዙሪያ ምላሽ ያልሰጠች ሲሆን፤ አል-ዐይን ኒውስ ከውጭ ጉዳይ እና የመንግስት ኮሙንኬሽን ጉዳዮች ምላሽ ለማግኘት ያደረግነው ሙከራ አልተሳካም።