ኢትዮጵያ “የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት ወደ ድንበሬ ዘልቀው በመግባታቸው ነው” አለች
የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት በሚሊሸዎች መሆኑን ኢትዮጵያ አስታወቀች
ሱዳን ስም ከማጉደፍ ተግባሯ ልትታቀብ ይገባል ስትልም ኢትዮጵያ አስጠንቅቃለች
የሱዳን ወታደሮች የተገደሉት በሚሊሸዎች መሆኑን የኢትዮጵያ መንግስት አስታወቀ።
ሱዳን ሰባት ወታደሮቿ በኢትዮጵያ ጦር እንደተገደሉባት መናገሯ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ማምሻውን ባወጣው መግለጫ በኢትዮ-ሱዳን ድንበር ከሰሞኑ በተፈጠረው የሱዳን ወታደሮች ሞት ማዘኑን አስታውቋል።
ሚኒስቴሩ በመግለጫው እንዳለው ድርጊቱ የተፈጠረው በሱዳን መከላከያ ሰራዊት እና በአካባቢው ባሉ ሚሊሻዎች መካከል መሆኑን ጠቅሶ በተፈጠረው የሱዳን ወታደሮች ሞት ማዘኑን ገልጿል።
ከአምስት ቀናት በፊት የሱዳን ጦር በህወሃት በመታገዝ ወደ ኢትዮጵያን ድንበር በመግባት ችግር ለመፍጠር ሲንቀሳቀሱ በሚሊሻዎች ጥቃት እንደደረሰባቸው የገለጸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫ ጉዳዩ በቀጣይ እንደሚመረመርም አስታውቋል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ ግን በሱዳን ጦር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ያወጧቸውን መግለጫዎች ተቀባይነት እንደሌላቸው ተገልጿል።
የሱዳን ጦር የኢትዮጵያን ድንበር ጥሶ ገብቶ ጥቃት ለመፈጸም ሞክሮ እያለ ያለ አግባብ የኢትዮጵያን ስም መነሳቱ ትክክል አለመሆኑን የገለጸው መግለጫው፤ ሱዳን ከድርጊቷ እንድትታቀብ አስጠንቅቋል።
በሱዳን በኩል እየተሰጡ ያሉ አሁናዊ መግለጫዎች በሁለቱ ሀገራት መካከል የነበረውን የረጅም ጊዜ ወዳጅነት የሚያበላሽ መሆኑንም የኢትዮጵያ ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
የሰሞኑ ክስተትም የሁለቱን ሀገራት መልካም ወዳጅነት ሆን ብለው የማበላሸት እቅድ ባላቸው አካላት መሆኑንም ኢትዮጵያ ትረዳለች ተብሏል።
ኢትዮጵያ የሁለቱ ሀገራት ልዩነቶች በመርህ ላይ የተመሰረቱ መፍትሄዎችን ለማምጣት ዝግጁ እንደሆነችም ተገልጿል፡፡
የሱዳን መከላከያ ቃል አቀባይ በትናንቱ መግለጫ እንዳለው “ሰባት የሀገሪቱ ጦር አባላት በኢትዮጰያ እንደተገደሉ እና የአጸፋ እርምጃ እንደሚወስድ” መናገራቸው ይታወሳል።
ይሄንን ተከትሎም የሱዳን ውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ዛሬ ባወጣው መግለጫ ጉዳዩን አስመልክቶ ለመንግስታቱ ድርጅት የጸጥታው ምክር ቤት እንደሚያመለክት አስታውቋል።
ከዚህ በተጨማሪም ሚኒስቴሩ ለሌሎች ዓለም አቀፍ፣ አህጉራዊና ክፍለ አህጉራዊ ተቋማት እንደሚያመለክትም ገልጿል።
እንዲሁም በካርቱም ያለውን የኢትዮጰያን አምባሳደር ለምን የሱዳን ጦር በኢትዮያ እንደተገደሉ ተጨማሪ ማብራሪያ እንደሚቀበልም ሚኒስቴሩ ዛሩ ባወጣው መግለጫ ጠቅሷል።