የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብና ዚምባብዌም ማዕቀቦቹ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲነሱ ጠይቀዋል
በዚምባብዌ ሪፐብሊክ ላይ የተጣለው ማዕቀብ በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንዲነሳ የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ጠየቁ።
ሙሳ ፋኪ ጥያቄውን ያቀረቡት የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) የፀረ-ማዕቀብ ቀን መታሰቢያን ቀንን እንደሚደግፉ ምክንያት በማድረግ ባስተላፉት መልእክት ነው።
የኮሚሽኑ ሊቀመንበር በዚምባብዌ ላይ የቀጠለው ማዕቀብ በሀገሪቱ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ልማት እንዲሁም የማገገም ጥረቶች ላይ የሚያሳድረው አሉታዊ ተጽእኖ እንደሚያሳስባቸውን ገልጸዋል።
ህብረቱ በቀጠናው የሚደረጉ ጥረቶችን ለመደገፍ ከደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) ጋር በቅርበት ለመስራት ቁርጠኛ እንደሆነም ነው ሙሳ ፋኪ ያረጋገጡት።
በዚህም የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) ሊቀ መንበርና የማላዊ ሪፐብሊክ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ያስተለለፉት ዚምባብዌን የተመለከተ መግለጫ የአፍሪካ ህብረት ይደግፋል ብለዋል።
ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ በሰጡት መግለጫ፤ የደቡብ አፍሪካ ልማት ማህበረሰብ (SADC) ለዚምባብዌ ያለውን አጋርነት ለማሳየት፤ በሀገሪቱ ተጥሎ የነበረውን የተራዘመ ማዕቀብ እንዲነሳ ጽኑ ፍላጎት አለው ሲሉ ተናግሯል።
የማዕቀቡ መነሳት በሀገሪቱ ከፍተኛ የሆነ የማህበረ-ኢኮኖሚ መነቃቃት ከመፍጠሩ ባሻገር ለቀጠናው ከፍተኛ ፋይዳ አለውም ብሏል የሳድክ ሊቀ መንበሩ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ።
ዚምባብዌ ካላት የኢኮኖሚ ድቀት እንድታንሰራራ እና የጀመረችውን የማገገም ሪፎርም እውን እንድታደርግ ዓለም አቀፍ የልማት አጋሮች በዚምባብዌ ኢንቨስት እንዲያደርጉም ጥሪ አቅርቧል።
በተጨማሪም የህግ የበላይነት፣ ዴሞክራሲ እና የሰብዓዊ መብቶች ጋር በተያያዘ ከሚመለከታቸው ዓለም አቀፍ አጋሮች ጋር ለመስራት ዚምባብዌም ሆነ ሳድክ ዝግጁ እንደሆኑ የሳድክ ሊቀ መንበሩ ፕሬዝዳንት ላዛሩስ ቻክዌራ ገልፀዋል።
የዚምባብዌው ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ በበኩላቸው፤ ለዚምባብዌ ልጆች ሲባል ማዕቀቡ ሊነሳ እንደሚገባ ጥሪ አቅረቧል።
ፕሬዝዳንት ምናንጋግዋ “ዛሬ በጋራ ተነስተን ይብቃን ብለናል፤ ህገ-ወጥ ማዕቀቡ ለዚምባብዌ ህዝቦች ልማት፣ ደህንነት እና ብልጽግና ማናቆ ነው። ዩናይትድ ስቴትስ ለልጆቻችን ሲባል ማዕቀቡን በአስቸኳይ እና ያለምንም ቅድመ ሁኔታ እንድታነሳ እንጠይቃለን"ም ብሏል።
ዚምባብዌ እንደፈረንጆቹ በ2000 መጀመርያዎች በአሜሪካ እና አውሮፓ ህብረት አማካኝነት የተጣለባትን ማዕቀብ ተከትሎ በከፍተኛ የማህበረ ኢኮኖሚ ቀውስ ተዘፍቃ የቆች ሀገር ናት።
በዚህም ከነጻነት በኋላ ባላት ሀብት “የአፍሪካ የዳቦ ቅርጫት” ትሆናለች ተብላ ስትጠበቅ የነበረችው ዚምባብዌ ከምዕራቡ ዓለም ጋር ያላትን ግንኙነት እጅጉን እየሻከረ በመምጣቱ “ለክፈተኛ የውጭ ምንዛሪ እና ገንዘብ እጥረት” የተጋለጠች ሀገር እንድትሆን ዳርጓታል።
ዚምባብዌ የቅኝ ግዛትን ቀምበር በመስበር እንደፈረንጆቹ ሚያዝያ 18/1980 ነጻነቷ የተቀዳጀች ሀገር እንደሆነች ይታወቃል።