አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውን ማዕቀብ እንድታነሳ የአፍሪካ ህብረት ጠየቀ
ማዕቀቡ ኩባ በመንግስታቱ ድርጅት የተቀረጸውን ዘላቂ የልማት ግቦችን እንዳታሳካ እንቅፋት መሆኑንም ነው ህብረቱ የገለጸው
በኩባ ላይ የተጣለው ማዕቀብ ትክክል አይደለም ሲል ህብረቱ አሳስቧል
አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችውን መዕቀብ እንድታነሳ የአፍሪካ ህብረት ጠየቀ፡፡
የአፍሪካ ህብረት ባወጣው መግለጫ አሜሪካ በኩባ ላይ የጣለችው ማዕቀብ እንዲነሳ ጠይቋል፡፡
አሜሪካ ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት ማብቂያ በኋላ ከተከሰተው የቀዝቃዛው ጦርነት ጀምሮ በኩባ ላይ የንግድ፣ የጦር መሳሪያ ግዢ እና ሌሎች ማዕቀቦችን ስትጥል ቆይታለች፡፡
አሜሪካ በጎረቤቷ ኩባ ላይ ማዕቀብ የጣለችው የአሜሪካውያንን ደህንነት የሚጋፉ የንግድ እና የጦር መሳሪያ ሽያጮችን ከተለያዩ ሶሻሊስት አገራት ጋር ያልተገቡ ግንኙነቶችን እያደረገች ነው በሚል ነበር፡፡
ይሁንና ይህ የአሜሪካ ማዕቀብ በፕሬዘዳንት ባራክ ኦባማ የስልጣን ዘመን የሁለቱ አገራት ግንኙነት መሻሻል ያሳየ ቢመስልም ፕሬዘዳንት ዶናልድ ትራምፕ ወደ ስልጣን ሲመጡ በፈረንጆቹ 2017 ማብቃት የነበረበት ማዕቀቡ እንዲራዘም ወስነዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረትም በኩባውያን ላይ የተጣለው ማዕቀብ ሊነሳ ይገባል ሲል ጥያቄውን አቅርቧል፡፡
ማዕቀቡ በኩባውያን ላይ የተወሰነ ህገወጥ ድርጊት ነው ያለው ህብረቱ ኩባውያን ከዓለም ጋር ንግድ እና ኢንቨስትመንት እንዳያካሂዱ እንቅፋት መሆኑንም አስታውቋል፡፡
ማዕቀቡ አሜሪካ ኩባዊያን ከተቀረው ዓለም ጋር የንግድ እና ፋይናንስ ወዳጅነት እንዳይመሰርቱ ያደረገ ኢ ፍትሃዊ ውሳኔ በመሆኑ አሜሪካ የጣለችውን ማዕቀብ ልታነሳ ይገባልም ብሏል፡፡
ህብረቱ አክሎም የአሜሪካ ማዕቀብ ኩባ ከኮሮና ቫይረስ ጉዳት እንዳታገግም የሚያደርግ የጭካኑ ውሳኔ መሆኑንም ገልጿል፡፡
እንዲሁም የአሜሪካ ማዕቀብ ኩባዊያን በመንግስታቱ ድርጅት የተረቀቀውን የዘላቂ የልማት ግቦችን ለማሳካት እንዳይችሉ ያደርገልም ያለው የአፍሪካ ህብረት ሁሌም ከኩባዊያን ጎን እንደሚቆም አስታውቋል፡፡