የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ ጥር ላይ መፈጸሙ ይታወሳል
የአሜሪካ የሕግ መወሰኛ ምክር ቤት 2 ነጥብ 2 ቢሊየን ዶላር የሚያወጡ የጦር መሳሪያዎችን ለግብፅ እንዲሸጥ ወሰነ።
ዋሸንግተን ለካይሮ የምትሸጥላት የጦር መሳሪያዎች ሲ- 130 የተባሉ የጦር አውሮፕላኖች መሆናቸውን ሮይተርስ ዘግቧል።
የሕግ መወሰኛ ምክር ቤቱ ይህንን የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነትን ያጸደቀው በ81 ድጋፍ እና በ18 ተቃውሞ እንደሆነም ተገልጿል።
አሜሪካ ለግብፅ በምትሸጠው የጦር መሳሪያ ላይ ተቃውሞ ያቀረቡ አባላት ጥያቄዎችን አቅርበዋል ተብሏል። አባላቱ ተቃውሞውን ያቀረቡት ጉዳዩን ከሰብዓዊ መብቶች አለመከበር ጋር በተያያዘ እንደሆነም ነው የተገለጸው።
ተቃውሞ ካቀረቡት መካከል የሪፐብሊካን ሴናተሪ ራንድ ፓውል አንዱ ሲሆኑ፤ ስምምነቱ ውድቅ እንዲደረግ ሞክረው ነበር ተብሏል።
በርካታ የዴሞክራት ፓርቲ ሴናተሮች ከሪፐብሊካኑ ተወካይ ጎን በመቆም ስምምነቱ ውድቅ እንዲደረግ ሞክረው ነበር ተብሏል።
ተቃዋሚዎቹ የአሜሪካ ኩባንያዎች የሰብዓዊ መብትን በመጣስ ብዙ ክብረ ወሰን ላለባቸው ሀገራት የጦር መሳሪያ መሸጥ እንደሌለባቸው ማንሳታቸውን ዘገባው ያመለክታል።
የአሜሪካ ፕሬዝዳንት ጆ ባይደን የመሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ ጥር ላይ ከተደረገ በኋላ ሀገራቸው በግብፅ የሰብዓዊ መብት ሁኔታን ካላሻሻለች ስምምነቱን እንደሚይዙት ገልጸው ነበር።
ባይደን ይህንን ያሉት የ130 ሚሊየን ዶላር ሽያጭ ስምምነትን በተመለከተ በሰጡት አስተያየት ነው ተብሏል።
የጦር መሳሪያ ሽያጭ ስምምነቱ የጦር አውሮፕላኖችን፤ አጋዥ መሳሪዎችን እና የጥገና መሳሪያዎችን እንዲሁም የቴክኒክ ድጋፍን ያካትታል።
ይህንን የጦር መሳሪያ ሽያጭ በዋናነት የሚያከናውነው ሎክሄድ ማረቲን የተባለ ኩባንያ መሆኑም ተገልጿል።