የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር ማኪ ሳል በዩክሬን ጉዳይ ከአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ
ማኪ ሳል በቅረቡ ዩክሬን እና ሩሲያን ለመጎብኘት ቃል መግባታቸው ይታወሳል
ውይይቱ በግጭቱ ምክንያት በተፈጠረው “የምግብ ችግር” ላይ ያተኮረ ነበር ተብሏል
የወቅቱ የአፍሪካ ህብረት ሊቀ መንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል፤ በሩሲያ ዩክሬን ጦርነት ዙሪያ ከአውሮፓ ምክር ቤት አባላት ጋር ተወያዩ፡፡
ጦርነቱን ተከትሎ ባጋጠመው የምግብ አቅርቦት ችግሮች ላይ ያተኮረ ነበር የተባለለት የበይነ መረብ ውይይቱ ትናንት ማክሰኞ ነው የተካሄደው፡፡
ማኪ ሳል ዩክሬንን እና ሩሲያን የመጎብኘት ፍላጎት እንዳላቸው ማስታወቃቸው ይታወሳል፡፡ ውይይቱ ይህንኑ ተከትሎ የተካሄደ ስለመሆኑም የፕሬዝዳንቱ ጽ/ቤት አስታውቋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ በእቅዳቸው መሰረት ሩሲያ እና ዩክሬንን የሚጎበኙ የሁለቱንም ሀገራት መሪዎች እንደሚያገኙና ጦርነቱን ጨምሮ ወደ አፍሪካ ስለሚገቡ የምግብ ፍጆታዎች ጉዳይ እንደሚያወሩ ይጠበቃል፡፡
ከፍተኛ የምግብ ፍጆታዎች ላኪ የሆኑት ሩሲያ እና ዩክሬን ጦርነት መጀመራቸውን ተከትሎ ከፍተኛ ይልኩ የነበረው ምርት ቆሟል፡፡ በዚህም በመላው ዓለም ከፍተኛ የምግብ እጥረት አጋጥሟል፡፡ በእጥረቱ በዋናነት የአፍሪካ ሃገራት በተለይም ግብጽን መሰል ከፍተኛ የዩክሬን ስንዴ ተጠቃሚ ሃገራት ተጎድተዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ቭላድሚር ፑቲንን አደነቁ
የአፍሪካ ህብረት በዩክሬን ጉዳይ ዓለም አቀፍ ህግጋት እንዲከበሩ በማሳሰብ ለጦርነቱ ሰላማዊ መፍትሄዎች ይፈለጉለት ሲል መግለጫ ማውጣቱ ይታወቃል፡፡ የህብረቱ ሊቀመንበር ከወር በፊት ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ መወያየታቸውም እንዲሁ የሚታወስ ነው፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከውይይቱ በኋላ እንዳሉት ፑቲን ሀገራቸው ከዩክሬን ጋር የገቡበትን ጦርነት በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውኛል ያሉ ሲሆን ተስፋ ማድረጋቸውን ገልጸው ነበረ፡፡
አፍሪካ እንደ ህብረት ሩሲያ ዩክሬንን መውረሯን በመግለጽ ድርጊቱ በይፋ እንድታወግዝና ከምዕራባውያን ጋር እንድትወግን ይጠበቅ ነበረ፡፡ የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በህብረቱ ንግግር ለማድረግ መጠየቃቸውም ይታወሳል፡፡
ሆኖም ህብረቱ ጉዳዩ ሰላማዊ እልባት እንዲያገኝ ከማሳሰብ ውጭ በይፋ ሩሲያን አውግዞ የገለጸውም ሆነ ያንጸባረቀው አቋም የለም፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን በአባልነት እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ ከከ3 ወራት በፊት ለልዩ ዘመቻ በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን አስገብታለች፡፡ ድርጊቱ በርካታ ሀገራት በሩሲያ ላይ ማዕቀቦች እንዲያዘንቡ ምክንያት እንደሆነም የሚታወቅ ነው፡፡