ዜሌንስኪ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ዲሜትሮ ኩሌባ በኩል ነው ጥያቄውን በድጋሚ ያቀረቡት
የዩክሬን ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ በአፍሪካ ህብረት ንግግር ለማድረግ በድጋሚ ጠየቁ፡፡
ዜሌንስኪ በውጭ ጉዳይ ሚኒስትራቸው ዲሜትሮ ኩሌባ በኩል ነው ጥያቄውን በድጋሚ ያቀረቡት፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት ከዩክሬን የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዲሜትሪ ኩሌባ ጋር በስልክ ማውራታቸውን አስታውቀዋል፡፡
ለሙሳ ፋኪ የደወሉት ኩሌባ ፕሬዝዳንት ቮሎዲሚር ዜሌንስኪ ለአፍሪካ ህብረት አባል ሃገራት መሪዎች ንግግር ለማድረግ ከአሁን ቀደም ያነሱትን ጥያቄ ደግመው አንስተዋል፡፡
ከህብረቱ ጋር ጠንካራ ግንኙነት ለመመስረት እንፈልጋለን ስለማለታቸውም ነው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ የገለጹት፡፡
ሙሳ ፋኪ በበኩላቸው ዩክሬን ከሩሲያ ጋር ለገባችበት ጦርነት ሰላማዊ መፍትሔዎች ሊፈለጉለት እንደሚገባ አስረግጠው መናገራቸውን ገልጸዋል፡፡
I received a call from #Ukraine foreign minister @DymytroKuleba. He renewed a request from president Zelenskyy to address @_AfricanUnion Heads of State & his wish to develop closer ties with the AU. I insisted on the need for a peaceful solution to the conflict with #Russia.
— Moussa Faki Mahamat (@AUC_MoussaFaki) April 28, 2022
ፕሬዝዳንት ዜሌንስኪ ከአሁን ቀደም ከአዲሱ የህብረቱ ሊቀመንበር ከሴኔጋሉ ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ጋር በነበራቸው የስልክ ቆይታ በህብረቱ ንግግር ለማድረግ ጠይቀው ነበር፡፡
ሆኖም ጥያቄው ተቀባይነት ስለማግኘቱ አልታወቀም፡፡ ህብረቱ ፍቃድ ስለመስጠቱ ያሳወቀው ነገርም የለም፡፡
ዜሌንስኪ ዩክሬንን ደግፈው ሩሲያን አጥብቀው ባወገዙና የተለያዩ የማዕቀብ እርምጃዎችን በወሰዱ የተለያዩ ሃገራት ምክር ቤቶች የበይነ መረብ ንግግሮችን አድርገዋል፡፡
ሆኖም እስካሁን በህብረቱም ሆነ በአባል ሃገራቱ ያደረጉት ንግግር የለም፡፡ ልክ እንደነ አሜሪካ እና የአውሮፓ አጋሮቿ ሁሉ በይፋ ሩሲያን አውግዘው ተቃውሟቸውን ሲገልጹም ሆነ እርምጃዎችን ሲወስዱ የታዩ የህብረቱ አባል ሃገራትም የሉም ከኬንያ በስተቀር፡፡ ይህም ምዕራባዊ ሃገራትን ደስ አላሰኘም፡፡
አፍሪካ አቋሟን በይፋ እንድታሳውቅና ጠንካራ ምላሾችን እንድትሰጥም በአሜሪካ ጭምር ውትወታዎች ሲደረጉ ቆይተዋል፡፡
ኢትዮጵያ ሁኔታዎችን በአንክሮ እየተከታተለች መሆኑን በመግለጽ ሁሉም አካላት ከድርጊታቸው እንዲታቀቡ መጠየቋ ይታወሳል፡፡