የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል ቭላድሚር ፑቲንን አደነቁ
ፕሬዝዳንት ፑቲን ለውይይት ዝግጁ መሆናቸው ከዩክሬን ጋር የገቡበትን ጦርነት ለማቆም ያስችላልም ብለዋል
የሴኔጋል ፕሬዝዳንት እና የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ማኪ ሳል የሩሲያው ፕሬዝዳንት ፑቲን ለውይይት ዝግጁ መሆናቸውን አድንቀዋል
የአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር እና የሴኔጋል ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ቭላድሚር ፑቲንን አደነቁ፡፡
ማኪ ሳል ከሩሲያው ፕሬዝዳንት ቭላድሚር ፑቲን ጋር በስልክ መወያየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ፕሬዝዳንቱ ከውይይቱ በኋላ እንዳሉት ፑቲን ሃገራቸው ከዩክሬን ጋር የገቡበትን ጦርነት በውይይት ለመፍታት ዝግጁ መሆናቸውን ነግረውኛል ብለዋል፡፡
ይህን ያደነቁት ፕሬዝዳንት ማኪ ሳል ይህ መሆኑ የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነትን ሊያስቆም ይችላል ሲሉም አክለዋል፡፡
ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ቃል ኪዳን ጦርን በአባልነት እቀላቀላለሁ ማለቷን ተከትሎ ሩሲያ ከሁለት ሳምንት በፊት ለልዩ ዘመቻ በሚል ጦሯን ወደ ዩክሬን አስገብታለች፡፡
ይህ የሩሲያ ድርጊትም ከበርካታ አገራት ማዕቀቦችን እንዲጥሉባት ምክንያት የሆነ ሲሆን ሩሲያ በበኩሏ የአጸፋ እርምጃ እንደምትወስድ አስታውቃለች፡፡
አሜሪካ የሩሲያ ነዳጅ ወደ አገሯ እንዳይገባ እገዳ ያስተላለፈች ሲሆን ሩሲያም የአንድ በርሜል ነዳጅ ዋጋ በዓለም አቀፍ ገበያ አሁን ካለበት 140 ዶላር ወደ 300 ዶላር ሊያሻቅብ ይችላል ስትል አስጠንቅቃለች፡፡
ሩሲያ በዩክሬን እያደረገች ያለውን “ወታደራዊ ተልዕኮ” የአፍሪካ ሀገራት እንዲያወግዙ የአሜሪካ ውጭ ጉዳይ መስሪያ ቤት መጠየቁ ይታወሳል፡፡
ምንም እንኳን ብዙ የአፍሪካ ሀገራት የተባበሩት መንግስታት ድርጅትን የውሳኔ ሃሳብ ቢደግፉም አሁንም ሌሎች ሀገራት ሩሲያን ማውገዝ እንዳለባቸው ዋሸንግተን ጠይቃለች። የፖለቲካ አዋቂዎች የአፍሪካ ሀገራት ስለጦርነቱ ጥቂት ነገር ብቻ እያሉ መሆኑን ገልጸዋል።
ዓለም አቀፍ ማህበረሰብ አሁን ላይ በአንድ ላይ ሆኖ ድምጹን እያሰማ መሆኑን የገለጸችው አሜሪካ፤ ይህም ሉዓላዊነትን፣ ግዛታዊ አንድነትን፣ ግጭቶችን በሰላም መፍታትን እና የንጹሃንን ህይወት መታደግን የሚጠይቅ እንደሆነ አስታውቃለች፡፡