የተመድ ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ አዲስ አበባ ገብተዋል
በጉባኤው ከጉቴሬዝ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሸል ተሳታፊ ይሆናሉ ተብሏል
ጉተሬዝ በነገው እለት በሚጀመረው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸሃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ለመሳተፍ ትናንት ማምሻውን አዲስ አበባ ገብተዋል፡፡
ጉተሬዝ በነገው እለት በሚጀመረው የህብረቱ የመሪዎች ጉባኤ መክፈቻ ላይ ንግግር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዋና ጸሃፊው ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪች እንደተናገሩት፤ የአፍሪካ ነጻ የንግድ ቀጠና ትግበራ ፣የአህጉሪቱ ሰላም እና የጸጥታ ስጋቶችን ፣በአህጉሪቱ የሚሰተዋሉ ከአየር ንብረጥ ለውጥ ጋር የተያያዙ ቀውሶች ጉተሬዝ በንግግራቸው ከሚያነሷቸው ዋነኛ ጉዳዮች ናቸው፡
ዋና ጸሃፊው በዛሬው እለት ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት ጋር ተገናኝተው በተለያዩ የአህጉሪቱ አንኳር ጉዳዮች ላይ መክረዋል፡፡
የኮሚሽኑ ሊቀ መንበር ከጉተሬዝ ጋር ውጤታማ ውይይት ማድረጋቸውን በትዊተር ገጻቻው ባሰፈሩት ጽሁፍ ገልጸዋል፡፡
ሊቀ መንበሩ ሙሳ ፋኪ “ከዋና ጸሃፊው ጋር በአህጉሪቱ የተገኙትን ድሎች ወደ ኋላ የሚመልሱትን አንገብጋቢ የሰላም እና የጸጥታ ችግሮችን ለመፍታት ባለን የጋራ ቁርጠኝነት ላይ ውጤታማ ውይይት አድርገናል” ብለዋል፡፡
በተጨማሪ ዋና ጻሃፊው በሚኖሯቸው የጎንዮሽ ስብሰባዎች በሳህል እንዲሁም በዴምክራቲክ ኮንጎ ያለውን ሁኔታ በተመለከተ ይመክራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤው ከጉቴሬዝ በተጨማሪ የአውሮፓ ህብረት ምክር ቤት ፕሬዝዳንት ቻርልስ ሚሸል ተሳታፊ እንደሚሆኑም ተገልጿል፡፡
የተለያዩ የአፍሪካ ሀገራት መሪዎች፣ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ድርጅቶች እና ሀገራት ተወካዮች በ36ኛው የአፍሪካ ህብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ ለመሳተፍ የዲፕሎማተክ ማህበረሰብ ማዕከል ወደ ሆነችው አዲስ አበባ እየገቡ ስለመሆናቸው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ ያመለክታል።
አስካሁን አዲስ አበባ ከገቡት የአፍሪካ መሪዎች መካከል የደቡብ ሱዳን፣ የሩዋንዳ፣ የጊኒ ቢሳዎ፣ የሌሴቶ፣ የሊቢያ፣ የታንዛኒያ፣ ዴሞክራቲክ ኮንጎ እና የኮትዲቯር መሪዎች ይገኙበታል።
የደህንነት እና የምግብ እጥረት ችግሮች ላይ ትኩረት ሰጥቶ የሚመክረው ጉባኤው የአህጉሪቱ ዜጎችን ኑሮ ለማሻሻል ይበጃሉ ያላቸውን በተለያዩ ፖለቲካዊ እና ማህበራዊ-ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ቁልፍ ውሳኔዎችን ያሳልፋል ተብሏል፡፡
በተጨማሪም የአፍሪካ መሪዎች በምስራቃዊ ዲሞክራሲያዊ ኮንጎ ሪፐብሊክ ስላለው ግጭት እንዲሁም እአአ 2021 እና 2022 መፈንቅለ መንግስት ባስተናገዱ በማሊ፣ በቡርኪና ፋሶ፣ በጊኒ እና በሱዳን ስላለው የደህንነት ሁኔታ ገለጻ እንደሚደረግላቸው ሮይተርስ ዲፕልማቲክ ምንጮቹን ጠቅሶ ዘግቧል፡፡