ፖርቹጋላዊው አንቶንዮ ጉተሬዝ የተመድ ዋና ጸኃፊ በመሆን ለሁለተኛ ጊዜ ተመረጡ
አንቶንዮ ጉተሬዝ የተመረጡት 15 አባላት ካሉት የተመድ ጸጥታው ም/ቤት በቀረበ ምክረ ሀሳብ ነው
አሁን በዓለም ላይ የተደቀኑት ፈተናዎች የጉተሬዝ ከባድ የቤት ስራ እንደሚሆኑም እየተነገረ ነው
193 አባል ሀገራት ያቀፈው የዓለም ድርጅት በዛሬው ዕለት ባካሄደው ጠቅላላ ጉባኤ አንቶኒዮ ጉተሬዝን ለሁለተኛ ጊዜ ዋና ጸሐፊ አድርጎ መርጠዋል፡፡ ምጫውን ተከትሎ ጉተሬዝ ለሚቀጥሉት አምስት ዓመታት በኃላፊነት እንደሚያገለግሉም ነው የተገለጸው፡፡
አንቶንዮ ጉተሬዝ የተመረጡት 15 አባላት ካሉት የተመድ ጸጥታው ም/ቤት በቀረበ ምክረ ሀሳብ ነው፡፡
የኢኳደሩ ቀድሞ ፕሬዝዳንት ሮሳልያ አርቴጋን ጨምሮ ሰባት የሚሆኑ ሰዎች ለተመድ ዋና ጸሀፊነት የማመልከቻ ደብዳቤ ቢያስገቡም ም/ቤቱ ፖርቹጋላዊውን ጉተሬዝን ብቸኛ እጩ አድረጎ ማቅረቡን አሶሼትድ ፕሬስ ዘግቧል፡፡
በጉባኤው የተለያዩ ሀገራትን ከወከሉ አምባሳደሮች በተጨማሪ የሀገረ ፖርቹጋል ፕሬዝዳንት ማርሴሎ ሬቤሎ ዲ ሳውሳ ተገኝተዋል፡፡
አንቶንዮ ጉተሬዝ እንደተመረጡ ወዲያውኑ ቃለ መሃላ የፈጸሙ ሲሆን “አሁን ያለውን የጂኦግራፊያዊ ክፍፍል እና የተበላሸ የኃይል ግንኙነቶችን ለማሸነፍ የተቻለንን ሁሉ ለማድረግ” እንትጋ ሲሉ የድርጅቱን አባል ሀገራት ማሳሰብ አዘል ጥሪ አቅረበዋል፡፡
“ያልተመጣጠኑ ሚዛኖች እና ተቃርኖዎች በጣም ብዙ ናቸው እናም እንዚህ በሂደት መፍትሄ ሊበጅላቸው ይገባል”ም ነው ያሉት ጉተሬዝ፡፡
ጉተሬዝ “ዛሬ እየኖርን ያለነው የአለመተማመን ነገር እንደ ጽንስ የሚወርድ ነው፣ ነገር ግን መደበኛ ሊሆን አይችልም” ሲሉም አሁን ላይ በዓለም ፊት የተጋረጡ ፈተናዎች እንዲሚፈቱ ያላቸውን ተስፋ አክለዋል፡፡
ትልቅ ትንሽ ሳይባል በሀገራት መካከል መተማመን እንዲነግስ እና የግንኙነት ጠንካራ ድልድይ እንዲገነባ እንዲሁም የማይቻሉ የሚመስሉ ነገሮች የሚቻሉ መሆናቸውን ለማሳየት ባላቸው ኃላፊነት እንደሚታትሩም ነው አንቶንዮ ጉተሬዝ ለጉባኤው ቃል የገቡት፡፡
የቀድሞ የዓለም አቀፉ የስደተኞች ኤጀንሲ አለቃ ጉተሬዝ በፈረንቹ 2017 የቀድሞ ዋና ጸሃፊ ባንኪ ሙንን በመተካት ወደ ኃላፊነት መምጣታቸው የሚታወስ ነው፡፡ ቀደም ባሉ ጊዝያት ትውልድ ሀገራቸው ፖርቹጋልን በጠቅላይ ሚኒስትርነት ማገልገላቸውንም ጭምር፡፡
ጉተሬዝ የተመረጡበት ወቅት ዓለም ከፍተኛ ግጭቶች እያስተናገደች ባለችበት፣ የአየር ንብረት ለውጥ ፈተና በሆነበት እንዲሁም ወረርሺኝ ኩፍኛ በተንሰራፋበት ወቅት ከመሆኑ ጋር ተያይዞ ሁለተኛው የአምስት ዓመት የኃላፊነት ዘመናቸው ቀላል እንደማይሆን ከወዲሁ እየተነገረ ይገኛል፡፡