ተመድ ለሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ክብረ ወሰን የሆነ 51 ነጥብ 5 ቢሊየን ዶላር ያስፈልገኛል አለ
የበጀት ጥያቄው ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪን ያሳያ ነው
በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ተጨማሪ 65 ሚሊየን ሰዎች እርዳታ ያስፈልጋቸዋል
የተባበሩት መንግስታት ድርጅትና አጋሮቹ ለፈረንጆቹ 2023 ክብረ-ወሰን የሆነ 51 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የእርዳታ ገንዘብ ለማግኘት ጥያቄ አቀረቡ።
በዓመቱ በአስር ሚሊዮኖች የሚቆጠሩ ተጨማሪ ሰዎች ሰብዓዊ እርዳታ ያስፈልጋቸዋል ተብሎ እንደሚጠበቅም ተመድ አስታውቋል።
የተመድ በሚቀጥለው የፈረንጆቹ ዓመት ተጨማሪ 65 ሚሊዮን ሰዎች እርዳታ እንደሚያስፈልጋቸው ግምቱን ያስቀመጠ ሲሆን፤ ይህም በ68 ሀገራት ሰብዓዊ እርዳታ የሚሹ ሰዎችን ቁጥር 339 ሚሊዮን ያደርሳል ነው የተባለው።
ይህም ማለት በምድር ከሚኖሩ ሰዎች አራት በመቶኛዎቹ ወይም የአሜሪካ አጠቃላይ ህዝብ ማለት ነው።
በዩክሬን ያለውን ጦርነት እና በአፍሪካ ቀንድ ድርቅን በመጥቀስ የተባበሩት መንግስታት የአደጋ ጊዜ እርዳታ አስተባባሪ ማርቲን ግሪፍትስ "የሰብዓዊ ፍላጎቶች በሚያስደንቅ ሁኔታ ከፍተኛ ነው። ምክንያቱም በዚህ ዓመት አስከፊ ክስተቶች ወደ 2023 እየተሻገሩ መሆናቸው ነው" ብለዋል።
በአፋፍ ላይ ላሉ ሰዎች ይህ የገንዘብ ጥያቄ የህይወት መስመር ነው ብለዋል።
ግጭት እና የአየር ንብረት ለውጥ የመፈናቀል ችግርን በማባባስ ከ100 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለዋልም ተብሏል።
ይህ በእንዲህ እንዳለ በሩሲያ እና በዩክሬን መካከል ለዘጠኝ ወራት የዘለቀው ጦርነት ወደ ውጭ የሚላኩ የምግብ ምርቶች እንዲስተጓጎሉ ማድረጉን እና በ37 ሀገራት ውስጥ ወደ 45 ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በአሁኑ ወቅት ለረሀብ ተጋልጠዋል መባሉን ሮይተርስ ዘግቧል።
የዘንድሮው የበጀት ጥያቄ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር የ25 በመቶ ጭማሪን ያሳያል።
የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በታሪኩ ትልቅ የገንዘብ ክፍተት ገጥሞታል የተባለ ሲሆን፤ እስከ ህዳር አጋማሽ ድረስ ባለው መረጃ መሰረት በፈረንጆቹ 2022 ያቀረበው የገንዘብ ጥያቄ መጠን 53 በመቶ ያህሉን ብቻ አግኝቷል።
"ስለዚህ የሰብዓዊ ድርጅቶች በተገኘው ገንዘብ ለማን እጅ መስጠት እንዳለባቸው ለመወሰን ይገደዳሉ" ሲል የተመድ መግለጫ ጠቅሷል።