አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአፍሪካ ስላሉ ግጭቶች ምን አሉ?
አንቶኒዮ ጉተሬዝ በአፍሪካ ስላሉ ግጭቶች ምን አሉ?
በ33ኛው የአፍሪካ ሕብረት የመሪዎች ጉባኤ ላይ የተገኙት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ዋና ጸኃፊ አንቶኒዮ ጉተሬዝ በሰጡት መግለጫ በአፍሪካ አህጉር ማለትም በደቡብ ሱዳንና በሊቢያ ያለው ግጭት እንደሚያሳስባቸው ገልጸዋል፡፡
ግጭቶቹን ለመፍታት ከአፍሪካ ህብረት ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሀመት ጋር መነጋገራቸውንም ተናግረዋል፡፡
ጉተሬዛ “ህዝባችሁን አስቡ፤ አክብሩ” በማለት ለደቡብ ሱዳን ተፋላሚ ወገኖች መልእክት አስተላልፈዋል፡፡
የደቡብ ሱዳን ዜጎች ጉዳት እየደረሰባቸው ነው፤ “የስደተኞች ኮሚሽን ውስጥ ስሰራ ምን ያህል ይሰቃዩ እንደነበር አውቃለሁ ብለዋል፡፡”
የሊቢያን ጉዳይ በተመለከተ አፍሪካ ህብረትና የተባበሩት መንግስታት ድርጅት በትብብር ለመፍታት ይሰራሉ።
በሊቢያ እርቅ እንዲኖርም በጋራ እንሰራለን ብለዋል ጉተሬዝ፡፡
ዋና ጸኃፊው የወቅቱ አንገብጋቢ ስለሆነውና በቻይና ሁዋን ግዛት ተከስቶ ወደ ተለያዩ ሀገራት እየተዛመተ ባለው ገዳይ የኮሮና ቫይረስ በሽታ ላይ መልእክት ያስተላለፉ ሲሆን፣ በመልእክታቸውም በበሽታው ዙሪያ በትብብር መስራት እንጂ ማግለል አይገባም ብለዋል፡፡
በአየር ንብረት ለውጥ አፍሪካ እየተጎዳች መሆኗንና የአንበጣ መንጋ በምስራቅ አፍሪካ ሃገራት እንደተከሰተ መስማታቸውንና ድጋፍ እንደሚያስፈልግ ዋና ጸኃፊው ተናግረዋል፡፡