የተመድ የስደተኞች ኤጀንሲ ከፍተኛ ኮሚሽነር በትግራይና አማራ ክልል ስለነበራቸው ቆይታ ምን አሉ?
ፍሊፖ ግራንዲ፤ ከሰላም ስምምነቱ በኋላ ተፈናቃዮችንና ስደተኞችን ለመደገፍ ተስፋ ሰጪ ሁኔታዎች መፈጠራቸው ተናግረዋል
ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፤ ኢትዮጵያ ስደተኞችን በማስተናገድ እየተወጣች ያለውን ዓለም አቀፍ ኃላፊነት አድንቀዋል
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በኢትዮጵያ በነበራቸው የሶስት ቀናት ቆይታ የትግራይ እና አማራ ክልሎችን ጎብኝተዋል፡፡
ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ቆይታቸውን በተመለከተ ለመገናኛ ብዙሃን በሰጡት መግለጫ፤ በመንግስት እና ህወሓት መካከል የተደረሰውን የሰላም ስምምነት ተከትሎ በኢትዮጵያ ተስፋ ሰጪ ነገሮች እንዳሉ ተናግረዋል፡፡
በትግራይ መቀሌ ቆይታቸው በጦርነቱ ምክንያት የተፈናቀሉ ሰዎች ማነጋገረቻውን የገለጹት ፍሊፖ ግራንዲ፤ ከተፈናቀሉት አብዛኞቹ ሴቶችና ህጻናት መሆናቸውም ገልጸዋል፡፡
“በርካታ ተፈናቃዮችን አናግሬያለሁ፤ ሁሉም የሚያነሱት ነገር ቢኖር ወደ ቤታችን መመለስ እንፈልጋለን የሚል ነው” ብለዋል ኮሚሽነሩ፡፡
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽን (ዩኤንኤችሲአር) እስካሁን 15ሺህ ተፈናቃዮችን ወደ አከባቢያቸው እንዲመለሱ ማድረጉም አስታውቀዋል፡፡
በቀጣይ ሁሉም ተፈናቃዮች ወደ መኖሪያ አከባቢያቸው ለመመለስ ከኢትዮጵያ መንግስት ጋር በጋራ እንደሚሰሩም ጭምር ተናግረዋል ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ፍሊፖ ግራንዲ፡፡
በመላ ሀገሪቱ ያሉ ተፈናቃዮችን ለማገዝ በሚቻልበት ዙሪያ ከፕሬዝዳንት ሳህለወርቅ ዘውዴ እና ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትሩና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ጋር መወያየታቸውንም ጭምር ገልጸዋል፡፡
ፍሊፖ ግራንዲ በሰሜን አከባቢ ስላለው የሰብዓዊ እርዳታ ስርጭት ሁኔታ ሲገልጹም፤ ያለው ችግር መጠነ ሰፊ እንደመሆኑ የስብዓዊ እርዳታን መጠንን ማሳደግ አስፈላጊ ነው ብለዋል፡፡
ተፈናቃዮች ወደ ቤታቸው ሲመለሱ ድጋፍ እንደሚስፈልጋቸውና ለዚህም አቅም እንደሚያስፈል የገጹት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፤ “ዓለም ለዚህ እጁ መዘርጋት አለበት” ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ኢትዮጵያ ያሏትን ችግሮች ለማቃለል መንግስት ከሚያደርገው ጥረት በተጨማሪ ዓለም አቀፍ ድጋፍ ያስፍልጋልም ነው ያሉት ፍሊፖ ግራንዲ፤ በደቡብ ኢትዮጵያ አከባቢ ያለውን ድርቅ እና በኦሮሚያ ያለውን ውጥረት እንደ አብነት በማንሳት፡፡
ኢትዮጵያ ከጦርነቱ በፊት ወደነበራት የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ መመለስ አለባትም ነው ያሉት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፡፡
የ“አለምዋጭ መጠለያ ጣቢያ” ጉዳይ
የተባበሩት መንግስታት የስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነር ፍሊፖ ግራንዲ በቆይታቸው ከጎበኝዋቸው ቦታዎች አንዱ ወደ 22 ሺህ የሚጠጉ የኤርትራ ስደተኞች ያሉበት በአማር ክልል ዳባት የሚገኘውን አለምዋጭ መጠለያ ጣቢያ ነው፡፡
አለምዋንጭ በደም አፋሳሹ የሰሜን ኢትዮጵያው ጦርነት ምክንያት በትግራይ ከሚገኙ መጠለያ ጣቢያዎች ሸሽተው የመጡ ኤርትራውያን ስደተኞች የሚገኙበት መጠለያ ጣቢያ መሆኑ ታወቃል፡፡
ይሁን እንጅ ስደተኞቹ ወደ መጠለያ ጣቢያው ከመጡ በኋላ ከደህንነት እና አቅርቦት ጋር የተያያዘ ችግር እንዳለባቸው በተለያዩ ጊዜያት ሲያነሱ ደማጣሉ፡፡
“ከስደተኞቹ እና የመጠለያ ጣቢያው ተወካዮች ጋር ሰአታት ወስጄ ተነጋግሬያለሁ” ያሉት ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፤ ስደተኞቹ የሚያነሷቸው ችግሮች እንዳሉ አምነው ችግሮቹ እንዲቀረፉ ዩኤንኤችሲአር ይሰራል ሲሉ ቃል ገብተዋል፡፡
በአለምዋጭ ከሚገኙ ኤርትራውያን ስደተኞች በተጨማሪ በአፋር በራሕሌ መጠለያ ጣቢያ እና በአዲስ አበባ የሚገኙ 70 ሺህ ያህሉ ኤርትራውያን ስደተኞችን ፤ ዩኤንኤችሲአር የተለያዩ ድጋፎች እያደረገ መሆኑም ጭምር ገልጸዋል፡፡
በመጨረሻም 880 ሺህ በላይ ስደተኞችን በማስተናገድ ዓለም አቀፍ ኃላገፊነቷን እየተወጣች ያለችውን ኢትዮጵያ ልትመሰገን ይገባል ብለዋል ከፍተኛ ኮሚሽነሩ፡፡
የዓለም አቀፉ ማህበረሰብ የኢትዮጵያ ጥረት ከግምት በማስገባት አስፈላጊውን ድጋፍ ሊያደርግ እንደሚገባም ጠይቀዋል፡፡
የሰላም ስምምቱ ኪዚህ በበለጠ ተግባራዊ እየሆነ ሲሄድ፤ የሚመሩት የተመድ ተቋም (ዩኤንኤችሲአር) ከሌሎች ለጋሽ ድርጅቶች ጋር በመሆን አዳዲስ ፕሮጀክቶች ተግባራዊ ለማድረግ እቅዶ እየተንቀሳቀሰ ነውም ብለዋል ተባበሩት መንግስታት ስደተኞች ከፍተኛ ኮሚሽነሩ ፍሊፖ ግራንዲ፡፡