በኢትዮጵያ የሚገኙት የሩሲያ እና ዩክሬን ኤምባሲዎች ከሰሞኑ አስተያየቶችን እየሰጡ ነው
የአፍሪካ ሕብረት ኮሚሽን ሊቀመንበር ሙሳ ፋኪ ማሃማት በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተደረገ ያለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት ጠየቁ፡፡
ኮሚሽን ሊቀመንበሩ ከሩሲያው ውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ጋር መነጋገራቸውን ገልጸዋል፡፡ ሙሳ ፋኪ ማሃማት፤ ከሰርጌ ላቭሮቭ ጋር ባደረጉት የስልክ ባደረጉት ውይይት ዓለም አቀፍ ሕግ እንዲከበር መጠየቃቸውን ይፋ አድርገዋል፡፡ ኮሚሽን ሊቀመንበሩ፤ በሩሲያ እና ዩክሬን መካከል እየተካሄደ ያለው ጦርነት ሰላማዊ መፍትሄ እንዲፈለግለት መጠየቃቸውን በይፋዊ የትዊተር ገጻቸው ላይ አስፍረዋል፡፡
የሩሲያው ውጭ ጉይይ ሚኒስትር ሰርጌ ላቭሮቭ ከሙሳ ፋኪ ማሃማት ጋር ስላደረጉት ንግግር በግልም ሆነ በመንግስት ገጾች ላይ ያስተላለፉት ነገር የለም ተብሏል፡፡
አሜሪካ ደግሞ የአፍሪካ ሀገራት ከዩክሬን ጎን እንዲቆሙ በተደጋጋሚ ስትወተውት መቆየቷ የሚታወስ ሲሆን ሀገራቱ ግን የተለያየ አቋም እያራመዱ ነው፡፡
ለአብነትም ሩሲያ እና ዩክሬንን በተመለከተ በተመድ በተዘጋጁ ስብሰባዎች ላይ የአፍሪካ ሀገራት ከሩሲያም ከዩክሬንም ጎን ቆመው ታይተዋል፡፡ በሌላ በኩል ከሰሞኑ በአዲስ አበባ የሚገኘው የሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ኢትዮጵያውያን ተሰልፈው መታየታቸው በርካቶችን አነጋግሯል፡፡
በዚህ ጉዳይ ላይ በኢትዮጵያ የሚገኙት የሩሲያ እና የዩክሬን ኤምባሲዎች ምላሾቻቻን ለአል ዐይን አማርኛ ሰጥተዋል፡፡ ሩሲያ ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄ እንደማትቀበል በኤምባሲዋ በኩል ስትገልጽ፤ ዩክሬን ደግሞ አልተሳካላትም እንጅ ሩሲያ ኢትዮጵያውያንን ለመመልመል እየሞከረች ነው ብላለች፡፡
ያም ሆነ ይህ አሁንም ከአፍሪካ ሀገራት ውስጥ የተወሰኑት ሩሲያን ቀሪዎቹ ደግሞ ዩክሬንን እየደገፉ ቀጥለዋል፡፡ ዩክሬን የሰሜን አትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ድርጅት (ኔቶ) ን ለመቀላቀል ፍላጎት ማሳየቷን ተከትሎ ሩሲያ እና ዩክሬን የጀመሩት ይፋዊ ጦርነት 56 ቀኑን ይዟል።