የሩሲያ ኤምባሲ፤ ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል አስታወቀ
የሩሲያ ጦር የትኛውንም ተልዕኮ በራሱ የመፈጸም አቅም እንዳለውም ነው ኤምባሲው ያስታወቀው
ኤምባሲው በራሷ በሩሲያ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ የተቀመጡ ህግጋትን እንደሚያከብር አስታውቋል
ለ‘ሩሲያ እንዝመት’ የሚሉ ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል በኢትዮጵያ የሩሲያ ኤምባሲ አስታወቀ፡፡
ኤምባሲው ለአል ዐይን አማርኛ በላከው መግለጫ፤ እ.ኤ.አ በ1961 በቬና የተፈረመውን ኮንቬንሽን እንደሚያከብርና ምንም አይነት የምልመላ ጥያቄዎችን እንደማይቀበል አስታውቋል፡፡
የቬናው ኮንቬንሽን የውጭ ሀገር ሰዎችን ለወታደራዊ ስራ መመልመል ክልክል መሆኑን እንደሚደነግግ ያስታወሰው ኤምባሲው ሩሲያም ድንጋጌዎቹን ታከብራለች ብሏል፡፡
ሩሲያ ያቀደችውን ሁሉ በራሷ ጦር በብቃት እንደምትፈጽም የገለጸው ኤምባሲው፤ በአጋርነት ለቀረቡና ለሚቀርቡ ጥያቄዎች ክብር እንዳለውም ገልጿል፡፡
ኤምባሲው ኢትዮጵያውያን በአካል እና በኢ-ሜይል በሚልኳቸው መልዕክቶች እያሳዩ ላሉት አጋርነት አመስግኖ መልዕክቶቹ የሁለቱን ሀገራት ‘የማይሰበር’ ወዳጅነት የሚያሳዩ መሆናቸውን ገልጿል፡፡
ኢትዮጵያ በተባበሩት መንግስታት ድርጅት የሰብአዊ መብቶች ምክር ቤት ጉባዔ ላይ ሩሲያን ለማገድ የቀረበውን የውሳኔ ሀሳብ መቃወሟ ይታወሳል፡፡ ሩሲያን ደግፋ ድምጽ መስጠቷም አይዘነጋም፡፡ለዚህም ኤምባሲው ምስጋና አቅርቧል፡፡
ከሰሞኑ በማህበራዊ ትስስር ገጾች በርካታ ኢትዮጵያውያን ወጣቶች በሩሲያ ኤምባሲ በር ላይ ተሰልፈው ታይተዋል፡፡ ይህን ተከትሎ በርካቶች ወጣቶቹ ከሩሲያ ጎን ተሰልፎ ለመዋጋት መሰለፋቸውን ሲገልጹ ነበር፡፡
የሩሲያ ኤምባሲ ፕሬስ አታሼ ትናንት ከአል ዐይን አማርኛ ጋር ባደረጉት ቆይታ ምንም አይነት ምልመላ እየተካሄደ እንዳልሆነ ገልጸው ነበር፡፡ በአዲስ አበባ የሚገኘው የዩክሬን ኤምባሲ ደግሞ ሩሲያ ኢትዮጵያውያንን ለመመልመል እየሞከረች እንደሆነ ለአል ዐይን አማርኛ አስታውቋል፡፡