የአፍሪካ ህብረት መንግስት እና ህወሓትን የሚያደራድሩ ግለሰቦችን ማንነት ይፋ አደረገ
መንግስት እና ህወሓት በደቡብ አፍሪካ በሚካሄደው የሰላም ድርድር ለመሳተፍ ፈቃደኛ መሆናቸው አስታውቀዋል
አፍሪካ ህብረት መንግስትና ህወሓት በኢትዮጵያ ሰላም እንዲሰፍን ያሳዩት ቁርጠኝነት በደስታ እንደሚቀበለው ገልጿል
የአፍሪካ ህብረት ከቀናት በፊት ለህወሓትና መንግስት በላከው ደብዳቤ የሁለቱም ወገኖች ተወካዮች በደቡብ አፍሪካ ተገኝተው ልዩነቶቻቸውን በድረድር እንዲፈቱ ጥሪ ማቅረቡ ይታወሳል።
ጥሪውን ተከትሎም የኢትዮጵያ መንግስት እና ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር በደቡብ አፍሪካ ውስጥ ለሚካሄደው የሰላም ድርድር የቀረበላቸውን ግብዣ መቀበላቸውን አስታውቀዋል፡፡
የአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃማት የትዮጵያ መንግስትና ህወሓት ጥሪውን በመቀበል ለድርድሩ ባሳዩት ቁርጠኝነት በደስታ እንደሚቀበሉት ግልጸዋል፡፡
የሰላም ድርድሩ በበላይነት የሚመራው በታዋቂ አፍሪካውያን ቡድን አማካይነት እንደሆነም ነው የገለጹት ሊቀ መንበሩ፡፡
የሰላም ድርድር ፓኔሉ የሚመራው በአፍሪካ ቀንድ የአፍሪካ ህብረት ከፍተኛ ተወካይና በቀድሞው የናይጄሪያ ፕሬዝዳንት ኦሊሴጎ ኦባሳንጆ ፣ በቀድሞው የኬንያ ፕሬዝዳንት ኡሁሩ ኬንያታ ፣በቀድሞ የደቡብ አፍሪካ ምክትል ፕሬዝዳንት ዶ/ር ፉምዚሌ ምላምቦ-ንጉካ እና የአፍሪካ ህብረት ባለሙያዎች ቡድን አማካኝነት ነውም ብለዋል፡፡
በአፍሪካ አህጉር ሰላም ማስፈን ወሳኝና አስፈላጊ ነው ያሉት ሊቀ መንበሩ፤ በሰሜን ኢትዮጵያ የተፈጠረውን ግጭት በዘላቂነት እና በድርድር ለመፍታት በሁለቱም ወገኖች መካከል ገንቢ ተሳትፎ እና ውይይት እንዲኖር በማድረግ በኩል በአደራዳሪዎቹ ሰፊ ልምድና የአመራር አቅም ሙሉ እምነት እንዳላቸውም ገልጸዋል ሙሳ ፋኪ፡፡
በተጨማሪም ሊቀ መንበሩ ሁለቱም ለድርድር የሚቀመጡ ወገኖች ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ እና ለሰፊው የአፍሪካ ቀንድ ቀጣና የሚጠቅም የሰላም እድል እንዲሰጡ በድጋሚ ጥሪ አቅርበዋል።
ሊቀመንበሩ አጋር ድርጅቶች በአፍሪካ ህብረት ለሚመራው ሂደት ቀጣይነት ያለው እሴት ጨምረው የሚያደርጉትን ድጋፍ አመስግነው በኢትዮጵያ ዘላቂ ሰላም ለማምጣት ከአፍሪካ ህብረት ጋር ያላቸውን አጋርነት እንዲያጠናክሩም ጠይቀዋል፡፡
በድጋሚ ጦርነቱ ከተቀሰቀሰ በኋላ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር ለመደራደር ፍቃደኝቱን የገለጸው ህወሓት ጌታቸው ረዳን እና ጄነራል ጻድቃን ገ/ትንሳኤን ያከተተ ተደራዳሪ ቡድን መሰየሙን ማስታወቁ ይታወሳል፡፡
የኢትዮጵያ መንግስት የአፍሪካ ህብረት ጥሪ መንግስት ከዚህ በፊት ሲያራምድ የነበረውን አቋም የጠበቀ ነው ብሏል፡፡
መንግስት ንግግሩ በአፍሪካ ህብረት አደራዳሪነት ብቻ እንዲሆንና ያለ ቅድመ ሁኔታ እንዲደረግ መንግስት አቋሙን ሲገልጽ ቆይቷል፡፡
ጦርነቱ በነሀሴ ወር ከመቀስቀሱ በፊት በአፍሪካ ህብረት የአደራዳሪነት ሚና ላይ ጥያቄ ሲያነሳ የነበረው ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር ለመደራደር እንደሚፈልግ ከሳምንት በፊት ማስታወቁ ይታወሳል።
የኢትዮጵያ መንግስት በሽብር ከፈረጀው ህወሓት ጋር የገባው ጦርነት ከተጀመረ ሁሉት አመቱን እያገባደደ ነው።