የፌደራል መንግስትና ህወሓት ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ወደ ድርድር እንዲገቡ አሜሪካ ጠየቀች
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእከተኛው የኢትዮጵያ ቆይታን አስምልከቶ መግለጫ አውጥቷል
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት በድርድር ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ መግለጹን በአዎንታ እንደምትቀበለው አስታውቃለች
የፌደራል መንግስትና ህወሓት ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ ወደ ድርድር እንዲገቡ የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ጠየቀ።
የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልዕክተኛ የሆኑት አምባሳደር ማይክ ሀመር በኢትዮጵያ በነበራቸው ቆይታ ዙሪያ መግለጫ አውጥቷል።
በመግለጫውም የአሜሪካ መንግስት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእከተኛ የሆኑት አምብሳደር ማይክ ሀመር ዳግም የተቀሰቀሰው ጦርነት በአፈጣኝ ማቆም በሚቻልበት ዙሪያ ከኢትዮጵያ መንግሰት፣ ከህወሓት እና ከአፍሪካ ህብረት አመራሮች ጋር ለመምከር ነሃሴ 30 ቀን 2014 ዓ.ም አዲስ አበባ መድረሳቸውን አስታውቋል።
እስከ መስከረም 6 2015 ድረስ በአዲስ አበባ በነበራቸው ቆይታም ጦርነት እንዲቆም እና ወደ ድርድር እንዲገባ ለማስቻል ከተለያዩ አካላት ጋር መምከራቸው የተገለፀ ሲሆን፤ ይህንን የዲፕሎሲ ስራ በኒው ዮርክ እየተካሄደ ባለው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት ጠቅላላ ጉባዔ ላይ እንደሚቀጥሉም የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
አምባሳደር ማይክ በአዲስ አበባ ቆይታቸው ከአሜሪካ ኤምባሲ ጉዳይ ፈጻሚ ትሬሲ አን ጃኮብሰን ጋር በመሆን ከጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ እና ከምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር እና የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን ጋር ተገናኝተው መወያየታቸውም ተመልክቷል።
በውይይታቸውም በሰሜን ኢትዮጵያ ዳግም ያገረሸውን ጦርነት እና ኤርትራ ወደ ግጭቱ ተመልሳ መግባቷን ተከትሎ አሜሪካ ባላት ስጋት ዙሪያ እንዲሁም ግጭቱ በአፋጣኝ ቆሞ ችግሮች በአፍሪክ ህብረት መሪነት በሚካሄደው ድርድር በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት በሚቻልበት ዙሪያ መምከራቸው ተገልጿል።
ልዩ መልእክተኛው ከአፍሪካ ህብረት የአፍሪካ ቀንድ ልዩ መልእክተኛ ኦሊሴንጉን ኦባሳንጆ ጋር አሜሪካ በአፍሪካ ህብረት ጥላ ስር የሚካሄደውን ድርድር መደገፍ ነምትችልበት ጉዳዮች ላይ መክረዋል የተባለ ሲሆን፤ እንዲሁም ከተመድ እና ከአውሮፓ ህብረት ተወካዮች ጋር እንደተወያዩም ተገልጿል።
በተጨማሪም ልዩ መልእከተኛው ከአፍሪካ ህብረት ኮሚሽን ሊቀ መንበር ሙሳ ፋኪ መሃመት፣ ከኢትዮጵያ ፍትህ ሚኒስትር ጌዲዮት ጤሞጢዮስ (ዶ/ር) እንዲሁም ከጠቅላይ ሚኒስትሩ የብሄራዊ ደህንነነት አማካሪ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን ጋር መወያየታቸውም ተመላክቷል።
አሜሪካ የኢትዮጵያ መንግስት በድርድር ለመሳተፍ ያለውን ዝግጁነት በድጋሚ መግለጹን እንዲሁም ህወሓት በአፍሪካ ህብረት ስር የሚካሄደውን ድርድር በመቀበል ያወጣውን መግለጫ በአዎንታ እንደሚቀበል የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር አስታውቋል።
በዚሁ መሰረት ሁሉም ወገኖች ተጨባጭ እርምጃ በመውሰድ በቅን ልቦና ወደ ድርድር እንዲገቡ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤቱ ጠይቋል።