የሶማሊያ መሪዎች “ለሶማሊያ ብሄራዊ ጥቅም ቅድሚያ እንዲሰጡ” ጥሪ ቀረበ
ተቋማቱ የሶማሊያ መሪዎች ለህዝባቸው ሲሉ “ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሀዊ እና ተዓማኒ ምርጫ” እንዲያካሂዱ ጠይቀዋል
የአፍሪካ ህረትን ጨምሮ ተመድ፣ የአውሮፓ ህብረት እና ኢጋድ በሶማሊያ ጉዳይ ላይ የጋራ መግለጫ አውጥተዋል
በፖለቲከኞቿ አለመስማማት ምክንያት በከፍተኛ ቀውስ ውስጥ ተዘፍቃ በምትገኘው “ሶማልያ” ላይ ያተኮረ ዓለም አቀፍ ምክክር ተደርጓል፡፡
በሶማሊያ አሁናዊ ሁኔታ ላይ ያተኮረውን ይህን ምክክር ያካሄዱት የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣ አፍሪካ ህብረት፣ አውሮፓ ህብረት እና የምስራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግስታት (ኢጋድ) ናቸው፡
የኢጋድ ዋና ፀሀፊ ወርቅነህ ገበየሁ(ዶ/ር)፣ በአፍሪካ ህብረት የፖለቲካ ጉዳዮች፣ሰላምና ፅጥታ ኮሚሽነር አምባሳደር ባንኮሌ አዶየ፣ በአውሮፓ ህብረት የአፍሪካ ማኔጂንግ ዳይሬክተር ሪታ ላራንጂነሀ እንዲሁም በተባበሩት መንግስታት የፖለቲካ እና የሰላም ግንባታ ጉዳዮች ዋና ፀሀፊ ሮስማሪ ዲካርሎም በምክክሩ ተሳትፈዋል፡፡
የተወያዩበትን ጉዳይ በተመለከተ ባወጡት የጋራ መግለጫ የሶማሊያ መሪዎች “ለሶማሊያ ብሄራዊ ጥቅም” ቅድሚያ እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ወሳኝ በሆኑ የልዩነት ጉዳዮች ላይ ከስምምነት እንዲደርሱ በቶሎ ወደ ውይይት እንዲመለሱም ነው ጥሪ ያቀረቡት፡፡
ፖለቲከኞቹ የሃገሪቱን መረጋጋት ሊያናጋ የሚችልን ምንም ዓይነት እርምጃ ከመውሰድ እንዲቆጠቡም አሳስበዋል፡፡
የሶማሊያ መረጋጋት ለዓለም ሰላም ወሳኝ መሆኑንም ነው ተቋማቱ በመግለጫቸው ያመላከቱት፡፡
ተቋማቱ “የመስከረም 17ቱ ስምምነት ሃገራዊ ምርጫውን በአጭር ጊዜ ለማካሄድ አዋጪው መንገድ ነው”ም ብለዋል፡፡
የሶማሊያ መሪዎች ለምርጫው ተፈፃሚነት ሲሉ የየካቲት 16ቱ የባይደዋ ቴክኒካል ኮሚቴ ምክረ ኃሳቦችን መልሰው እንዲገመግሙና ጥቅም ላይ እንዲያውሉም አሳስበዋል ተቋማቱ በመግለጫቸው፡፡
የሶማሊያ መሪዎች ዛሬ ላይ ለህዝባቸው የሚያደርጉት ነገር ቢኖር “ሰላማዊ፣ ነፃ፣ ፍትሀዊ እና ተአማኒ ምርጫ” ማካሄድ መሆኑን እንዲረዱ እና ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጡም ጭምር ጠይቀዋል፡፡
የሶማልያ መሪዎች ተቀራርበው በጋራ ጉዳዮቻቸው ላይ እንዲመክሩ የዓለም አቀፍ አጋሮች ሚና ከፍተኛ እንደሆነና ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ነው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት፣አፍሪካ ህብረት፣አውሮፓ ህብረት እና ኢጋድ የጋራ መግለጫ የሚያመለክተው፡፡
ከቀናት በፊት የተካሄደው የሶማሊያ ፖለቲከኞች ድርድር “ካለ ውጤት” መጠናቀቁ ይታወሳል፡፡
ይህም ሶማሊያን ለድጋሚ ቀውስ እንዳይዳርጋት ተሰግቷል፡፡
የምርጫ ኮሚሽን ምስረታ ፣የተገንጣይዋ የሶማሌላንድ ኮሚሽን አባላት ምርጫ እና በሶማሊያ-በኬንያ አዋሳኝ ድንበር (ጌዶ ክልል) ቀውስ ጉዳይ አሁንም በሶማሊያ ምድር ትልቅ ትኩረት የሚሹ አወዛጋቢና አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡
የፕሬዝዳንት ፋርማጆ ስልጣን የማራዘም ብሎም የምርጫውን የማዘግየት ፍላጎትም ራሱን የቻለ ተግዳሮት እንደሆነም ተቺዎች ይወቅሳሉ፡፡
የምርጫ ውዝግቡ ሶማሊያን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡
ይህም የቀጠናው አሸባሪው ቡዱን አልሻባብ እድሉን በመጠቀም ዳግም አንሰራርቶ የአፍሪካ ቀንድ የደህንነት ሁኔታን ያዳክማል በሚል በርካቶችን አስግቷል፡፡