የሶማሊያ ፖለቲከኞች ድርድር “ካለ ውጤት” ተጠናቀቀ
ምርጫን በተመለከተ በሃገሪቱ ፖለቲከኞች ዘንድ ያለው ውዝግብ ሶማሊያን ለድጋሚ ቀውስ እንዳይዳርጋት ተሰግቷል
መንግስት ለድርድሩ አለመሳካት የፑንትላንድ እና የጁባላንድ ክልል መሪዎችን ተጠያቂ አድርጓል
የፕሬዝዳንታዊ ምርጫውን መራዘም ተከትሎ ሶማሊያን ከገባችበት አጣብቂኝ ለማውጣት በሃገሪቱ ፖለቲከኞች የተደረገው ድርድር “ካለ ውጤት” ተጠናቀቀ፡፡
ድርድሩ በፕሬዝዳንት ሞሃመድ አብዱላሂ ሞሃመድ (ፋርማጆ) በሚመራው የፌዴራል መንግስት እና በክልል መንግስታት መሪዎች መካከል የተካሄደ ነበር፡፡
ሆኖም “ካለ ውጤት” ተጠናቋል እንደ ሃገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ኡስማን ዱቤ ገለጻ፡፡
ኡስማን ዱቤ ለድርድሩ አለመሳካት የፑንትላንድ እና የጁባላንድ ክልል መሪዎችን ተጠያቂ አድርገዋል፡፡
“የሁለቱ ክልል መሪዎች መስከረም 17/2020 እና የካቲት 16/2021 በተደረሱ ስምምነቶች መሰረት በሶማሊያ ምርጫ እንዲካሄድ ፍላጎት እንደሌላቸው ግልፅ አድርገዋል” ነው ሚኒስትሩ በጋዜጣዊ መግለጫቸው ያሉት፡፡
ክልሎቹ በበኩላቸው የፋርማጆን አስተዳደር ይወቅሳሉ፡
ዓለም አቀፉ ማህበረሰብ በፕሬዝዳንት በፋርማጆ እንዲሁም በክልል መሪዎቹ ላይ ከፍተኛ ጫና እያደረገ ባለበት በአሁኑ ወቅት ነው ድርድሩ ያልተሳካው፡፡
ይህ ባልተረጋጋ ሁኔታ ውስጥ ለምትገኘው ሶማሊያ ይበልጥ አሳሳቢ ጉዳይ እንደሆነ ነው አፍሪካን ኒውስ የዘገበው፡፡
የምርጫ ኮሚሽን ምስረታ ፣የተገንጣይዋ የሶማሌላንድ ኮሚሽን አባላት ምርጫ እና በሶማሊያ-በኬንያ አዋሳኝ ድንበር (ጌዶ ክልል) ቀውስ ጉዳይ አሁንም በሶማሊያ ምድር ትልቅ ትኩረት የሚሹ አወዛጋቢና አበይት ጉዳዮች ናቸው፡፡
የፕሬዝዳንት ፋርማጆ ስልጣን የማራዘም ብሎም የምርጫውን የማዘግየት ፍላጎትም ራሱን የቻለ ተግዳሮት እንደሆነም ተቺዎች ይወቅሳሉ፡፡
ፕሬዝዳንቱ ባለፈው የካቲት ወር የስልጣን ዘመናቸው አብቅቷል፡፡
የጁባላንዱ መሪ አህመድ ማዶቤ በክልላቸው የሚካሄደውን ምርጫ ሞቃዲሾ በበላይነት ትቆጣጠረው የሚለው ኃሳብ ይቃወማሉ፡፡
“ጁባላንድ እንደ ክልል የራሱን የምርጫ ኮሚቴ ሊሾም ሊፈቀድለት ይገባል”ባይም ናቸው፡፡ ይህ የአህምድ ማዴቦ ሀሳብ ግን በፕሬዝዳንት ፋርማጆ ተቀባይነት አላገኘም፡፡
የምርጫ ውዝግቡ ሶማሊያን የፖለቲካ ቀውስ ውስጥ እንድትወድቅ አድርጓታል፡፡
ይህም የቀጠናው አሸባሪው ቡዱን አልሻባብ እድሉን በመጠቀም ዳግም አንሰራርቶ የአፍሪካ ቀንድ የደህንነት ሁኔታን ያዳክማል በሚል በርካቶችን አስግቷል፡፡